ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ጉባኤ በመስከረም 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 17/2011 ኢትዮጵያ የገበያ ትስስር ለመፍጠር አመቺ መሆኗ ከግምት ገብቶ ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧ ተገልጿል። ጉባኤው በሸራተን አዲስ ሆቴል ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን የጉባኤው አዘጋጅ የቤንች ግሎባል ኢቨንት ማኔጅግ ዳይሬክተር ሚስተር ማቲው ቤይስ አስታውቀዋል። ጉባኤው ባለሀብቶችና ታዳጊ ባለሀብቶች በጋራ ሆነው በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ ያመቻቻልም ተብሏል። በተጨማሪም ተቋማት የንግድ መለያቸውን የሚያስተዋውቁበት፤ የልምድ ልውውጥና ንግድን በተመለከተ ምክክር የሚደረግበት እንዲሁም የገንዘብ ምንጭ የማፈላለግ እድል የሚፈጠርበት ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ጉባኤው የቱሪዝም መዳረሻዎችን የምናስተዋውቅበት፤ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራትና ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግና አብሮ ለመሰራት የሚያስችል እድል የሚፈጠርበትም ነው ብለዋል። ጉባኤው አገሪቷ ያላትን የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ቅርሶችንና ሃብቶችን ለአለም ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛትም ተገልጿል። የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ድርጅቶችና አገራት ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና የተሻለ ስራ በመስራት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ይቻላልም ብለዋል። የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው በመንግስት በኩል የቱሪዝም መዳረሻዎች ተለይተው አለም አቀፍ መለያ ካላቸው አገሮችና ድርጅቶች ጋር ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ጉባኤው የሀገራችንን ገፅታ የምናስተዋውቅበት፤ በዘርፉ የተሻለ ስራ ለመስራት ህብረተሰቡን የምናነቃቃበት፤ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለይተን በማውጣት የማስተካከያ ስራ የምንሰራበትና ኢንቨስተሮችን የምንጋብዝበት ነውም ብለዋል። "ልምድ ካላቸው የዘርፉ አለም አቀፍ ተዋናዮች ጋር ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር የጠበቀ ትስስር ፈጥረን የተሻለ ስራ የምንሰራበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንም ይጠበቃል" ብለዋል። ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር እና የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ስራ ለመስራት አይነተኛ መፍትሄ ነውም ብለዋል። ጉባኤው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን በመገንባት እና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በማፍራት የቱሪዝም ዘርፉ ማምጣት ያለበትን ውጤት እንዲያመጣ የሚያግዝ እንደሚሆንም ነውየገለፁት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም