ቀጥታ፡

''የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ)የሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል''-ሊቀመንበሩ

ጅግጅጋ ሐምሌ 17/ 2011 የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ)ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ሊቀመንበሩ አስታወቁ። ፓርቲው 21ኛው ምስረታ በዓሉን "የሕግ የበላይነት፤ ዴሞክራሲና ጠንካራ አገረ መንግሥት ለላቀ ለውጥ!" በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ አከብሯል። የፓርቲው ሊቀ-መንበር አቶ አህመድ ሺዴ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ፓርቲው የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ ጥረቱን ይቀጥላል። ፓርቲው በተያዘው በጀት ዓመትም  እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የሕዝብ ችግሮችን ለመፍታት  ይሰራል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው ሰላምና መረጋጋት የተረጋገጠው በትጥቅ ትግል ለይ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦብነግ) የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ በመግባቱ እንደሆነም  አስታውቀዋል። የድርጅቱ መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም ብለው  ለወሰዱት ውሳኔና ለተገኘው ውጤት አቶ አህመድ አመስግነዋል። "በክልሉ ትጥቅ ትግል የሚያካሄድ አንድም ድርጅት የለም" ያሉት ሊቀመንበሩ፣በዚህ ምክንያት የክልሉ ሕዝብ አንድነቱ እንዲጠናከርና በልማት ላይ ለማተኮር አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለታል  ብለዋል። ፓርቲው አገሪቱ የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት ለሕዝቦች አንድነት አማራጭ እንደሌለው በማመን እንዳይደናቀፍና እንዳይቀለበስ ጠንክሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችም የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ ለሰላም መከበርና ለልማት መረጋገጥ ድርሻቸውን  እንዲወጡም ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ(ኦብነግ) ሊቀመንበር አድሚራል መሐመድ ዑመር ፓርቲው በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የያዘውን ጥረት እንዲቀጥልበት አሳስበዋል። ድርጅታቸው  ወደ አገር  ለመመለስና የሰላም አማራጭን የተቀበለው ''ከሕዝባችን ጎን መቆማችንን ለማሳየት ነው''ብለዋል። ከፓርቲው ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ክልሉ ሰላሙን አረጋግጦ ልማት ላይ እንዲያተኩር ድርሻቸውን እንደሚወጡም አድሚራል መሐመድ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) የክልሎችና የፓርቲዎች አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ፓርቲው አጋጥሞት ከነበረው አደጋ ወጥቶ ወደ ትክክለኛ መሥመር በመግባት እየወሰዳቸው ላሉት እርምጃዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ግንባሩ ለአርብቶ አደሩ ሕዝብ ሕይወት ለማሻሻል ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም  አረጋግጠዋል። የፓርቲው መስራችና የቀድሞ ሊቀመንበር ሱልጣን ዓሊ ሸገህ  በበኩላቸው ወጣቶች ከፓርቲው ጎን በመቆም መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው፣በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች መረጃ በመመርመር እውነቱን ማወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) ተወካይ በበኩላቸው የኦሮሞና የሶማሌ ወንድማማች ሕዝቦችን ለማለያየት የተንቀሳቀሱ ጸረ ለውጥ ቡድኖች ባስነሱት ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመመለስ በኩል ፓርቲያቸው ከሶዴፓ ጋር በመሆን ድርሻውን  እንደሚወጣ አስታውቀዋል። በበዓሉ ላይ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ)ና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ(ሐብሊ) ተወካዮችና ለፓርቲው ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም