ቀጥታ፡

ለዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ የሚከለክለው አንቀጽ ክርክር አስነሳ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 17/2011 በምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ በዕጩነት ለሚቀርቡ የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ እንዳይከፈል የሚከለክለው አንቀጽ እንዲሻሻል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጠየቁ። ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በግብር ከፋዩ ህዝብ የሚያዘው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋል ስላለበት የመንግስት ሰራተኛ የሆነ ዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ደመወዝ አይከፈለውም ብሏል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዲስ በሚሻሻለው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች በአዋጁ ማንኛውም በዕጩነት የሚቀርብ የመንግስት ሰራተኛ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ደመወዝ አይከፈለውም የሚለው አንቀጽ 'መሻሻል አለበት' ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። የመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት አቶ መሣፍንት ሽፈራው በአዋጁ የመንግስት ሰራተኛ በዕጩነት ለምርጫ ውድድር ሲቀርብ በጊዜያዊነት ከስራ ገበታው መልቀቅ አለበት የሚለው አንቀጽ መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል። አንቀጹ የተማረውን የህብረተሰብ ክፍል ደሞዜን አጣለሁ በሚል ስሜት ከፖለቲካ ተሳትፎ ሊገድበው ይችላል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተወካይ አቶ ደጀኔ ጣፋ እንደተናገሩትም የመንግስት ሰራተኛ በዕጩነት ሲቀርብ  ደመወዝ አይከፈለው የሚለው አንቀጽ የተማረው ክፍል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቦታ እንዳይኖረው የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይህም ወደ ምክር ቤቱ በሚመጣው ተመራጭ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን አክለዋል። የምርጫ አዋጁ አካል ጉዳተኞች በምርጫ ተሳትፎና ሂደት መብታቸውን የሚያስከብር ሆኖ መጽደቅ ይኖርበታል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር ፌዴሬሸን ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ሁሴን ናቸው። ይህም አካል ጉዳተኞች እንደ ጉዳታቸው አይነትና ሁኔታ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ነው ያሉት። አቶ ወዳጄ ግርማ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ለአገር አቀፍ ፓርቲዎች 10 ሺህ አባላት ለክልል ፓርቲዎች ደግሞ 4 ሺህ የሚለው ቁጥር የተጋነነ ስለሆነ መቀነስ ይኖርበታል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በግብር ከፋዩ የሚበጀተው በጀት ለምርጫ ቅስቀሳና ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በዕጩነት የሚቀርብ የመንግስት ሰራተኛ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ 'ደመወዝ አይከፈለውም' ብለዋል። ይህም በህዝብ ሐብት ፣ ገንዘብና በተቋማት አደረጃጀት ላይ የተዛባ አስተሳሰብ እንዳይመጣ ከማገዙ ባለፈ የመንግስት ተቋማት ተዓማኒና ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ መንግስትና ፖለቲካን ለመለያየት ያስችላል ነው ያሉት። አንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ጠንካራ አማራጭ በመያዝና በማስተማር ዜጎችን በስፋት ማንቀሳቀስ ይኖርበታልም ብለዋል። በአዋጁ የተቀመጠው ቢያንስ ከአምስት ክልሎች 10 ሺህ ሰው የሚለው ከአገሪቷ የህዝብ ቁጥር አንጻር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው አገር አቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተቀመጠውን ቁጥር በሟሟላት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን የበለጠ ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። አዋጁ አካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ተሷትፎ ተደራሽ እንዲሆኑና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ ሳይቆራረጥ እንዲሰጥ ቦርዱ በንቃት እንዲሰራ እንደሚያስችለውም ተናግረዋል። አዋጁ ውይይት ተካሂዶበትና በቂ ግብዓት ተካቶበት የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ከመከፈቱ በፊት በአስቸካይ ስብሰባ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም