የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትማቸው ጋዜጦች ላይ የቅርጽና የይዘት ለውጥ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትማቸው ጋዜጦች ላይ የቅርጽና የይዘት ለውጥ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀ
ሐምሌ 17/2011 የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እለታዊዎቹን አዲስ ዘመንና ዘ-ኢትዮጵያ ሄራልድን ጨምሮ በሚያሳትማቸው ጋዜጦች ላይ የቅርጽና የይዘት ለውጥ እያደረገ ነው። ድርጅቱ በሱማልኛና ትግርኛ ቋንቋዎች ጋዜጦችን በማዘጋጀት በቅርቡ ለአንባቢያን ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታወቀ። ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው 78ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር በተከናወነው ስነ-ስርዓት ላይ ነው። በምስረታ በዓሉ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢዎች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የሚዲ ያሃለፊዎችና ባለሙያዎች፣ የድርጅቱ ሰራተኞች በተገኙበት “78 ዓመታትን በህዝብ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በድምቀት አክብሯል። በ1933 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጰያ ፕሬስ ድርጅት በአሁኑ ወቅት እለታዊ እና ሳምንታዊ ጋዜጦችን በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኦፋን ኦሮሞና አረብኛ ቋንቋዎች እያዘጋጀ የሚያሳትም መንግስታዊ የህትመት ሚዲያ ተቋም ነው። ከዚህም ሌላ "ዘመን" የተሰኘ መፅሄትም በየሁለት ወሩ በድርጅቱ እየተዘጋጀ ለንባብ ይበቃል። ድርጅቱ የይዘትና የቅርፅ ለውጥ ያደረገው በአማርኛ ቋንቋ በሚታተመው እለታዊው አዲስ ዘመን፣ የኢንግሊዝኛው ዘ_ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች እንዲሁም በሳምንት ሁለት ጊዜ በሚታተመው አፋን ኦሮሞ "በሪሳ" ጋዜጣ ላይ ነው። ለውጥ ማድረግ ያስፈለገው ህዝብና መንግስትን የሚያገናኙ ልዩ ልዩ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን በተሻለ መጠን በማንፀባረቅ ጋዜጦቹ በትክክል የህዝብ ድምፅ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ሲሉ የድርጅቱ የይዘት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ስዩም ተናግረዋል። የድርጅቱን የህትመት ውጤቶች ተደራሽነት ማስፋትም ለውጥ ለማድረግ የታሰበበት ሌላው ዓላማ መሆኑንም አክለዋል። ለጊዜው በዘ -ኢትዮጵያን ሄራልድ የእለተ እሁድ እና በአዲስ ዘመን ደግሞ የረቡእ እና ቅዳሜ ህትመቶች እንደዚሁም በበሪሳ ጋዜጣ የእለተ ቅዳሜ ህትመት ላይ ለውጥ መደረጉን ዶክተር ሄኖክ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ጋዜጦቹ ለአያያዝ በሚያመች መጠን፣ የአንባቢን ስሜት ሊስብ በሚችል ቅርጽ (ሌይአውት) እና የተለያዩ ሃሳቦችን በጥልቀት በሚተንትን ይዘት እንዲዘጋጁ እየተደረገ መሆኑን ነው ዶክተር ሄኖክ የገለፁት። በህትመቶቹ ላይ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ ከፍተኛ የይዘት መሻሻል እየመጣ መሆኑም በበዓሉ ላይ ተመልክቷል። በተለይም ህትመቶቹ በሀሳብ ብዝሃነትና የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚራመድባቸው መሆን መጀመራቸው በበጎነት ተነስቷል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው እንደገለጹት ድርጅቱ በ78 ዓመታት ጉዞ በዘመናት መካከል ተሻገሮ እዚህ ሲደርስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ድርጅቱ ሲሰራበት የቆየው የሚዲያ አደረጃጀት ዘመናዊ አለመሆን ገቢውን እንዳያሳድግ እንቅፋት ሆኖበት እንደነበር ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። በተለይም እስካሁን የራሱ የሆነ ማተሚያ ቤት የሌለው መሆኑ ተቋሙ በሚፈለገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል የሚሉት አቶ ጌትነት ሆኖም ድርጅቱ በአዲስ መልክ መቋቋም ይችል ዘንድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው አዋጅ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያስችለዋል ብለዋል። አዋጁ የራሱን ማተሚያ ቤቶች መገንባትን ጨምሮ ዘመናዊ የህትመት ሚዲያ አደረጃጀትን ለመፍጠር ብሎም የህትመቶቹን ተደራሽነት ለማጠናከር እንደሚያግዘው አክለዋል። የድርጅቱ ጋዜጠኞች በሚያዘጋጇቸው የተለያዩ ፅሁፎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልዩ እውቀት (እስፔሻላይዜሽን) እንዲኖራቸውና በተለዩ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ማድረግ ይቻል ዘንድም በየዘርፉ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል። ከዚህ በፊት በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ለህትመት ይበቃ የነበረው የአፋን ኦሮሞው ‘’ባሪሳ’’ ጋዜጣ የአንባቢያን ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲታተም መደረጉንም አመልክተዋል። በቅርቡም በሱማልኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ጋዜጦች ለንባብ ይበቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አፋን ኦሮሞና አረብኛ ቋንቋዎች የሚያሳትማቸው የህትመት ውጤቶች በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ስር በሚገኙ ዞንና ወረዳዎች አንዲሁም በውጭ አገር በኢትዮጰያ ኤምባሲና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ባሉባቸው የኣፍሪካ ፣ ኤሽያ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ ፣ ሰሜን አሜሪካ ይሰራጫሉ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከ350 በላይ ሰራተኞችን ይዞ በራሱ ገቢ የሚተዳደር አንጋፋ የህትመት ተቋም ነው።