በደቡብ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየቶች እያስተናገደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየቶች እያስተናገደ ነው
ዲላ/ሆሳዕና ኢዜአ ሐምሌ 17 ቀን 2011 በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ችግር ለማቃለል ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የጌድኦ ዞንና የሆሳእና ከተማ ነዋሪዎች የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል። ኮማንድ ፖስቱ ተጨባጭ የፀጥታ ስጋት በሌለባቸው አካባቢዎች አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ እንዲደረግ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል ። አስተያየታቸውን ከሰጡት የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች መካከል የባህል ጥናት ተመራማሪ አቶ ፀጋዬ ታደሰ በሰጡት አስተያየት በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ የፀጥታ ስጋቶችን ለመቆጣጠር ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ ተገቢ ነው ብለዋል። ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመስራትም ሆነ ሀብትና ንብረት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸው በተጣሰበት ሁኔታ በመደበኛው አሰራር ህግና ስርዓት ማስከበር ስለማይቻል ኮማንድ ፖስቱ መቋቋሙ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል። በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የፀጥታው ኃይል ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የማረጋጋት ስራ ሊያከናውን እንደሚገባም ተመራማሪው ጠቁመዋል ። የክልል እንሁን ጥያቄን ተገን አድርገው ህዝቡን በተለይ ወጣቱን ለእኩይ ተግባር ሲያንቀሳቅሱ በነበሩት የፖለቲካ አመራሮችንና ግለሰቦችን ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንጂ ፤ አካባቢው በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር መደረጉ ተገቢነት የለውም ያሉት ደግሞ ሌላው የጌዴኦ ዞን ነዋሪ አቶ ሄኖክ ጌታቸው ናቸው። በሰላም ወዳድ ህዝብ ላይ የታጠቀ ሃይልን ማሰማራት ዘላቂ ሰላም አያመጣም ያሉት አቶ ሄኖክ ፣ ህዝቡ የራሱን ሰላም እንዲጠብቅ እድል ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ካሰች ደንበል በበኩሏ በፀጥታ ችግር ምክንያት መንገዶች መዘጋታቸውን ተከትሎ በንግድ ስራው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን በመግለፅ የኮማንድ ፖስቱ መቋቋም የዘገየ መሆኑን ተናግራለች ። የሆሳእና ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኮማንድ ፖስቱ መቋቋም ለሰላም ያለው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አበራ ኢርሱሎ እንደተናገሩት የኮማንድ ፖስቱ መቋቋም መንግስት የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚያመለክት ተግባር ነው። አገር አፍራሽ ተልእኮ አንግበው የህዝብን ሰላም በማወክ አገራዊ ልማቱን ለማምከን የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች እንዳሉ ገልጸው ፣ ይህንን እኩይ ተግባር ለመቆጣጠር ኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። ህብረተሰቡም የሰላሙ ጠንቆች የሆኑ አካላትን አሳልፎ በመስጠት ከኮማንድ ፖስቱ ጎን መቆም ይጠበቅበታል ብለዋል ። ህግና መንግስት ባለበት ሀገር ማንኛውም አይነት ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ማራመድ እየተቻለ ወደ ሁከትና ብጥብጥ መግባት ተገቢነት የለውም ያሉት ደግሞ በከተማው የአራዳ ቀበሌ ነዋሪና የህግ ባለሙያ አቶ አበራ ቀልባሞ ናቸው። አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የኮማንድ ፖስት መቋቋም ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ወቅታዊም ተገቢ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። የጀሎ ነረሞ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት ሰላቶ በበኩላቸው ሰላም ሲጠፋ በይበልጥ ለጥቃት የሚጋለጡት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን በመግለፅ የኮማንድ ፖስቱ ለደህንነታችን አስፈላጊ ነው በማለት ገልፀውታል። ህጋዊ መስመርን ጠብቆ መጠየቅ እየተቻለ አገርን ለነውጥና ለጥፋት የሚዳርግ ተግባር መፈፀም ተቀባይነት የለውም ያሉት አስተያየት ሰጪ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል ።