በፀጥታ ማስከበር ተደራጅተን የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራን እውቅና ሊሰጠን አልቻለም - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በፀጥታ ማስከበር ተደራጅተን የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራን እውቅና ሊሰጠን አልቻለም - ወጣቶች
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 17/2011 በፀጥታ ማስከበር ተደራጅተን የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራን ቢሆንም እውቅና ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ በአዲስ አበባ የፈረንሳይ አካባቢ ወጣቶች ቅሬታ አቀረቡ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በቦታው ተግኘቶ በአካባቢው ስለነበረው የፀጥታ ችግር ያናገራቸው ወጣቶች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ መውጣትና መግባት ችግር እንደነበር ይናገራሉ። በተለይም አካባቢው ወጣ ያለና ጫካ ያለበት በመሆኑ ከተለያየ ቦታ እየመጡ ከጫት እስከ ካናቢስና ማሪዋና የመሳሰሉ አደገኛ ዕጽ ድረስ በመጠቀም ዘረፋ ያካሂዱ ነበር ይላሉ ። የኢዜአ ጋዜጠኛ በአካባቢው ባደረገው አሰሳም በተለያዩ ቦታዎች በህግ ክልክል የሆነው የማሪዋና አደንዛዥ እፅ ተዘርቶ እና አብቦ ማግኘት ችሏ። ይሁን እንጂ በዚህ ችግር የአካባቢው ነዋሪዎች በመማረራቸው የአካባቢውን ወጣቶች አወያይተው በተራ እንዲጠብቁ የማድረግ ስራ ከተጀመረ 6 ወራት ማለፉም ታውቋል። ይህንን የበጎ አድራጎት ተግባር የወረዳው ፖሊስ እንዲያውቀው ተደርጎም እንቅስቃሴ በመጀመሩ ምክንያትም ወጣቶቹ በዘረፋና አደንዛዥ እፅ በመውሰድ ላይ የተሰማሩ ግልሰቦችን መከላከል መቻላቸውንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ለዘረፋ ተደራጅተው የነበሩ ቡድኖች መበተናቸውንና ግማሾቹንም ለህግ ማቅረብ በመቻሉ አካባቢው አንፃራዊ ሰላም ማግኘቱንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ይሁንና በፈቃዳቸው ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ፀጥታ በመጠበቅ የተሰማሩት ወጣቶች ጥበቃውን ስንሰራ ህጋዊ ባጅ ወይም መታወቂያ ስላልተሰጠን ችግር እየገጠመን ነው ይላሉ። ለዚህም ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን ከ3 ወር በፊት ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አልተሰጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ፍትህ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ኩማ በበኩላቸው የወጣቶቹ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረው እስካሁን የዘገየው የሚሰጣቸውን ባጅ ወይም መታወቂያ ለህገ ወጥ ተግባር እንዳያውሉት ጥንቃቄ የማድረግ ስራ ሲሰራ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ማስከበር የተሳተፉት ወጣቶች ፎቶ ለፅህፈት ቤቱ መድረሱንና እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስም ባህሪያቸው ተጠንቶ መታወቂያው እንደሚሰጣቸውና ከቀጠናው ፖሊስ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ተናግረዋል።