ቀጥታ፡

በአርባ ምንጭና በአክሱም ከተሞች የተካሄዱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርና ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

አርባምንጭ/አክሱም ሰኔ 4/2010 በአርባ ምንጭና በአክሱም ከተሞች ዛሬ የተካሄዱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርና  ከፍተኛ ሊግ  ጨዋታዎች የተገናኙት ክለቦች በአቻ ውጤት ተለያዩ፡፡ በ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በደቡብ ደርቢ ጨዋታ አርባ ምንጭ ከነማ በሜዳው ወላይታ ዲቻን አስተናግዷል፡፡ አዞዎቹ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የጦና ንቦች ደግሞ ደረጃቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ባካሄዱት ፍክክር ከሁለቱም ወገን ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ሳይታይ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃ ስቀረው የዲቻ አስር ቁጥሩ ኢዮብ ዓለማየሁ በአርባ ምንጩ አሌክስ አሙዙ ላይ በፈጸመው ጥፋት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል፡፡ የአርባ ምንጭ ከነማ ተወካይ አሠልጣኝ ጃክሰን ፊጣ በሰጡት አስተያየት"  ለማሸነፍ ተዘጋጅተን ነበር ነገር ግን ተቃራኒ ቡድን ተከላክሎ በመጫወቱ ያሰብነው አልተሳካም "ብለዋል ፡፡ የወላይታ ዲቻ አሠልጣኝ ዘነበ ፍሰሃ በበኩላቸው " በውጤት ቀውስ ዉስጥ በመሆናችን በጥንቃቄ ብንጫወትም ማሸነፍ ካልቻልን ደግሞ ውጤት ለማስጠበቅ መከላከልና መልሶ ማጥቃትን መርጠናል" ብለዋል ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  በ20ኛው  ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ "ሀ" በአክሱም ከተማ ሜዳ የተገናኙት አክሱም እና ስሑል ሽረ እንዳስላሰ ክለቦች በአቻ ውጤት ተለያይተዋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱም ክለቦች ጨዋታ ባለሜዳው አክሱም ከተማ  በ16ኛ ደቂቃ ፍጹም ቅጣት አግኝተው ሺመክት ግርማ ወደ ግብ በመቀየር አንድ ለባዶ እየመራ እረፍት ወጥተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የስሑል ሽረ እንዳስላሰ  በ46ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ ግሩም ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም