"የአገራዊ ችግኝ ተከላ ተሳትፏችን ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ለመሆን ነው" - አረጋውያን - ኢዜአ አማርኛ
"የአገራዊ ችግኝ ተከላ ተሳትፏችን ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ለመሆን ነው" - አረጋውያን
አዲስ አበባ፤ ኢዜአ፤ ሐምሌ 17/2011 አረጋውያን በሀገራዊ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም መሳተፋቸው ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ለመሆን እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ለወጣቱ አርአያ ለመሆን በሚያስችል መልኩ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ አረጋውያን ተናግረዋል።
በእለቱ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ በሚጠይቀው “አረንጓዴ አሻራ” በሚል በሚካሄደው የችግኝ ተካላ ፕሮግራም መንገድ ዳር ቦታ በመረከብ 40 ችግኝ ተክለው አሻራቸውን ለማስቀመጥ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ያረጋል አለሙ ናቸው።
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋለ ያለውን የደን ልማት መመናመንን ለመከላከል ወጣቱ ትውልድ ወሳኝ ሚና አለው ያሉት አቶ ያረጋል፤ "አረጋውያን ባለን አቅም ችግኝ ተከላ ላይ ስንሳተፍ ለወጣቱ ትውልድ ተምሳሌት ወይም አርአያ ለመሆንና ለማስተማር ነው" ብለዋል፡፡
በእለቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አሻራ ሊያስቀምጥ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ በበኩላቸው ለአንድ አገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የአረንጓዴ ልማት መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ችግኝ መትከል መልካም ቢሆንም የእንክብካቤው ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አዛውንቶች በችግኝ ተከላ ተሳትፎ ሲያደርጉ ለወጣቱ ትውልድ መነሳሳት በመፍጠር “እኔስ” የሚል ጥያቄ በማጫር ወደ ስራ ለመግባት ይገፋፋቸዋል ይላሉ፡፡
እሳቸውም በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ አሻራቸውን ለማስቀመጥ ከወዳጆቻቸው ጋር ቀጠሮ እንደያዙ ተናግረዋል።
ስለ ደን፣ አትክልትና እፅዋት አስፈላጊነት ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ መምህር አብዲሳ አጋ፤ በአገሪቷ የትምህርት ስርዓት በማካተት ከስር መሰረቱ ከተሰራ ህብረተሰቡ ችግኝ ተክሎ መመለስ ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ የማሳደግ ልምድ እንዲያዳብር ያግዛል ነው ያሉት።
አረጋውያን ችግኝ ተከላ ላይ ተሳተፎ ሲያደርጉ ወጣቶቹ ቢያዩ በበለጠ ተነሳሽነት አደራ ተቀብለው እንዲሰሩ ጉልበት ይሆኗቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የ58 አመት ባለፀጋ የሆኑት መምህር አብዲሳ አጋ ገና በለጋ እድሜያቸው የጀመሩት የችግኝ ተከላ ለ50 አመታት በተከታታይ ቢያንስ በየአመቱ 5 ችግኝ እንደሚተክሉ ተናግረዋል፡፡
አሁንም በመንግስት ደረጃ ጥሪ የተደረገበት አገራዊ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ በግንባር ቀደምትነት አሻራቸውን ለማስቀመጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
“አረጋውያን ያልገቡበት የልማት ስራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአረጋውያን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ፤ በአገራዊው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ለመሳተፍ መዘጋጀታቸው ትውልዱን ከአረንጓዴ ልማት ጋር የማስተሳሰርና አርአያ ለመሆን አላማ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አረጋውያን ወጣቱ ትውልድ የልማት ዋና መሪና ሀገር ወዳድ እንዲሆን፤ ልማቱን ለቀጣይ ትውልድ እንዲያቆይ የማሰተማር ሃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
በርካታ ችግኝ በመትከል የአገሪቱ የደን ሽፋን እንዲሻሻል ማድረግ ከውበትና አገር ገፅታ ግንባታ ባሻገር፤ በደን መመናመን ምክንያት የሚመጡትን ችግሮች ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ጊዜያት በተፈጥሮ የደን ይዞታ የተሻለች እንደነበረች ና አሁን የሚስተዋለው በረሃማነትም ደኑን በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ ነው ያሉት።
የነገ ትውልድ የሚቀረጸው በምክር ብቻ ሳይሆን አረጋዊያን በተግባር ጭምር ማሳየት ስችሉ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከችግኝ ተከላ ተሳትፎ ባሻገር ወጣቱ በስሜት ተገፋፍቶ ወደ ጥፋት መንገድ እንዳያመራ አእምሮን የማልማትና አቅጣጫ የማስያዝ ግዴታ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።