የኮሌራ በሽታን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ዕቅድ እየተዘጋጀ ነው

55
ሀምሌ 14/2011 (ኢዜአ) የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝን በአስር ዓመት ውስጥ ማጥፋት የሚያስችል ብሔራዊ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የጤና ሚኒስቴር ከዓለም የጤና ድርጅትና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመሆን በብሔራዊ ዕቅዱ ዙሪያ ምክክር አድርጓል። በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ 986 ሰዎች ተጠቂ መሆናቸው ይታወቃል። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ በሽታው በስፋት የተገኘባቸው ሥፍራዎች ናቸው። የጤና ሚኒስቴርም ይህንን ከግምት በማስገባት የበሽታውን ስርጭት በአስር ዓመት ውስጥ ለማስቆም ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔውን ያሳለፈው ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት የኮሌራ ወረርሽኝን ለማስቆም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአስር ዓመት ስትራቴጂ መንደፉን ተከትሎ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው አሁን ላይ ከፍተኛ የኮሌራ በሽታ ስርጭት የሚታይባቸውን 20 አገራት አሉ። በዚህም መሰረት ድርጅቱ ቢቻል እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2030 በሽታውን የማጥፋት ዓለማ አንግቧል። አሊያም ደግሞ በበሽታው ምክንያት የሚሞተውን ሰው ቁጥር በ90 በመቶ ለመቀነስ ግብ ጥሏል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ከበደ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ይህን ዓለም አቀፍ ዕቅድ በብሔራዊ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ወስናለች። በአሁኑ ወቅትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ብሔራዊ ዕቅዱ ምን መምሰልና እንዴት መተግበር እንዳለበት ውይይት ተጀምሯል። የኮሌራን በሽታ በዘላቂነት ለማጥፋት የበርካታ ተቋማት ርብርብ ስለሚያስፈልግ ውይይቱ መካሄዱን ጠቅሰው ቀጣይነት እንዳለው ፍንጭ ሰጥተዋል። ይህም የተቋማትን ኃላፊነት ለመለየት፣ የሚያስፈልገውን ወጪና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች አጥርቶና ወስኖ ለመሄድ ይጠቅማል ነው ያሉት። የኮሌራ በሽታ በተበከለ ውሃና ምግብ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን በሽታውም በአብዛኛው ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ በሚታይባቸው ሥፍራዎች ላይ ይከሰታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም