በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ሱፐር ማርኬት ተመረቀ

ሀምሌ16/2011 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነና ሁሉንም ምርቶች በአንድ ማዕከል የያዘ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት በሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አማካይነት ተከፈተ። የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስራ አስኪያጅ ዶክተር አረጋ ይርዳው በምረቃው ወቅት እንዳሉት ሱፐርማርኬቱ በአይነቱ ለአገሪቷ የመጀመሪያ የሆነና ለሌሎች ተመሳሳይ ስራ ላይ ለተሰማሩት አረዓያ የሚሆን ነው። ሱፐርማርኬቱ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን መሰረት ባደረገ ዲዛይን የተሰራና ለደንበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ገልጸዋል። ዘመናዊና በመጠን ትልቅ ሆኖ የተሰራ ሲሆን የአግሮ ኢንዱሰትሪ ውጤቶች፣ የእርሻ ምርቶች፣ የባሕር ምግቦች፣ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች፣የታሸጉ መጠጦችና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶች የሚሸጡበት መሆኑንም ጠቁመዋል። የኩዊንስ ቀራንዮ ፕሮጀክት ጠቅላላ ወጪ 59 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ሲሆን የሚጠቀምበት ህንጻ የኤልፎራ አግሮ ኢንዱሰትሪ መሆኑንም ተናግረዋል። ከሌሎች ሱፐርማርኬቶች ልዩ የሚያደርገውም ዘመናዊ ዕቃ መደርደሪያዎች የተገጠሙለትና ምርቶቹም በ8 ዞኖችና በ20 ንዑስ የምርት ክፍሎች አቀማመጥ የተዘጋጁ መሆናቸውንም አንስቷል። የመሸጫ ዋጋን በባር ኮድ መጠቀም የሚያስችል ሲስተም ያለው የነዳጅ ማደያ፣ ካፌ፣ባንክና ሁለገብ አዳራሽ በአንድ አካባቢ የያዘና ደንበኞች በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። ዘመናዊ የምርት ማሳያና ማቆያና ማቀዝቀዣዎች የተገጠሙለት፣ለደምበኞች አመቺ የግብይት ሁኔታ ለመፍጠር በቂ የአየር መናፈሻዎች የተገጠሙለት እነዲሁም የመኪና መቆሚያ ስፍራ ያለው መሆኑም ከሌሎች ለየት ያደርገዋል። ኩባንያው ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት በማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ላይ ይገኛልም ተብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም