ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የቀደምት አባቶች የተጋድሎና የአንድነት ታሪክ በማስታወስ ለአገር ግንባታ እንዲረባረቡ የሕዝብ ተወካዮች ጠየቁ

ባህር ዳር ኢዜአ ሐምሌ 16/2011 ኢትዮጵያውያን የቀደምት አባቶች የተጋድሎና የአንድነት ታሪክ በማስታወስ ለአገር ግንባታ ሊረባረቡ እንደሚገባ የአማራና ሶማሌ ክልሎች የሕዝብ ተወካዮች አመለከቱ። በባህር ዳር ከተማ  በተካሄደው የሕዝብ ለሕዝብ የውይይት መድረክ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለኢዜአ እንደገለጹት ዜጎች የጋራ የሚያደርጋቸውን ታሪክ በመውሰድ አዲሲቱን ኢትዮጵያ መገንባት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚከፋፍል በእውነታ ላይ የተመሰረተ ታሪክ እንደሌለ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉትን አስተሳሰቦችን መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ሕዝቦች እርስ በርሳቸው እንዲጠራጠሩና ከመተባበር ይልቅ ወደ መለያየት የሚያመሩ ሃሳቦችን መከተል እንደማያስፈልግም ገልጸዋል። የሶማሌ ክልል የጎሳ መሪዎች ተወካይ ሱልጣን አብዱራሃማን ዱረሬእንደ ገለጹት ከሦስት ሺህ ዘመን በላይ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በሁሉም ዜጎች የጋራ ርብርብ ነው። በትብብር የተጠናከረችና ለሌሎች አፍሪካውያን ኩራት የሆነች አገርን በጋራ የገነባ ሕዝብ አሁንም አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባዋል ብለዋል። ሕዝቡ በሚነገረው ነገር ብቻ ሳይሆን እውነታውን ፈላጊና ምክንያታዊ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ወደ ባህር ዳር  የመጡትም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር መሆኑን አስታውቀዋል። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የተደረገው ውይይት ለሁለቱ ሕዝቦች ወንድማማችነት ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያም አንድነት ምሳሌነት ነው ያሉት ከአማራ ክልል የሃይማኖት አባቶች ተወካይ መላከ ሃይል ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ናቸው። በተለይ ባልሰራው ሥራ የማይገባውን ስምና ተግባር የተሰጠውን የአማራ ሕዝብ  እውነታ ለመረዳት የሶማሌ ክልል ሕዝብ እውነታውን ለማወቅ መምጣቱን ገልጸዋል። “የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እውነታውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ታሪክ በመረዳት ለሕዝቦች አንድነትና ለኢትዮጵያ መጠናከር እየሰሩ ስለሆነ ሌሎች መሪዎችም የእሳቸውን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል” ብለዋል። የሶማሌ ሕዝብ አቃፊና ካለው የሚያካፍል እንጂ፤ ባለፈው ዓመት የተወሰኑ ጨካኝና የሶማሌን ሕዝብ ባህልና ታሪክ የማይወክሉ ቡድኖች በክልሉ የፈጸሙትን እኩይ ተግባር አይወክልም ያሉት የአማራ ብሄር ተወላጅና በክልሉ ለረጅም ዓመታት የኖሩት የንግዱን ማህበረሰብ የወከሉት አቶ ስንታየሁ እሸቱ ናቸው። ሕዝቡ ከመሪዎች የሚነገረውን ነገር መስማት ብቻ ሳይሆን እውነታውን በራሱ መመርመር ይጠበቅበታል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ አንዱ ሌላኛውን የበደለ ሕዝብ የለም የሚሉት አቶ ስንታየሁ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰራጨውን ሕዝብን የማቃቃር ተንኮል በመረዳት በአንድነት ሊቃወም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የአማራና የሶማሌ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም