በሰሜን ሸዋ 192 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር ተሸፈነ

82
ደብረብርሃን ኢዜአ ሐምሌ 9 ቀን 2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት 192 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው ለኢዜአ እንደገለፁት እስካሁን ታርሶ በዘር የተሸፈነው መሬት በምርት ወቅቱ ለማልማት ከታቀደው 509ሺህ 816 ሄክታር ውስጥ ነው ። በምርት ወቅቱ ከሚለማው መሬት ውስጥ 38ሺህ 167 ሄክታሩ በመስመርና 43ሺህ 400 ሄክታሩ ጥቁር አፈር በማጠንፈፍ በዘር የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል ። ለምርት ወቅቱ የሚያገለግል 133ሺህ 748ኩንታል ማዳበሪያና 8ሺህ 302 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል ። በመኽር እርሻው ከ329ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ናቸው ተብሏል። የአሳግርት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድሙ ሸዋንግዛው እንዳሉት የክረምቱ ዝናብ ቀድሞ በመግባቱ የዘር ስራቸውን ፈጥነው ጀምረዋል ። "ማዳበሪያንና ምርጥ ዘር ተጠቅሜ  በ1 ሄክታር ተኩል ማሳየ ላይ የዘራሁት የገብስ ቡቃያ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል ። ጸረ አረም ኬሚካል በመጠቀም ማሳቸውን እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ካለፈው ዓመት ጀምሮ የቢራ ገብስ ማልማት መጀመራቸውን የገለፁት ደግሞ የዓሣ ባህር ቀበሌ አርሶ አደር ቄስ ሙልየ ፍቃደ ናቸው ። "ዘንድሮም የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ በመሆኑ ማሳዬን በወቅቱ በዘር ሸፍኛለሁ" ብለዋል። በዞኑ በምርት ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት 16 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም