ቀጥታ፡

የውጭ አገር ተጓዦች በአገር ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የቱሪዝም ቦታዎችን መጎብኘት የሚችሉበት አሰራር ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም ኢትዮጵያ ገብተው ወደ ተለያዩ አገሮች የሚጓዙ የውጭ አገር ተጓዦች በቆይታቸው የቱሪዝም ቦታዎችን መጎብኘት የሚችሉበት የአሰራር ስርዓት ሰነድ እየተዘጋጀ ነው። ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚመክር መርሃ-ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። መርሃ-ግብሩ ተጓዦች በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘት የሚችሉበትን አሰራር ለመዘርጋት ያለመ ነው። የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ መንገደኞችን ያስተናግዳል። ይሁን እንጂ አየር መንገዱን ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በቆይታቸው አገሪቱን ተዘዋውረው የሚጎበኙበት አሰራር የለም። ተጓዦች በአዲስ አበባ እንደሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ የሚፈልጉትን የቱሪስት ቦታ እንዲጎበኙ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ሊዘጋጅ መሆኑን ገልጸዋል። ለጎብኚዎች ምቹና ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ከደንበኞች አስተያየት መሰብሰቡን ጠቁመዋል። ''ከሁለት ቀን ያልበለጠ ጊዜ ያላቸው ተጓዦች በአዲስ አበባ የቱሪስት መስህቦችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ይደረጋል'' ብለዋል። ከሁለት ቀን በላይ ለሚቆዩ መንገደኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ እና በክልሎች የአገር ውስጥ በረራ ተጠቅመው መጎብኘት የሚችሉበት ዕድል እንደሚፈጠር አስረድተዋል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሰረተ ልማት ለማሟላት እና ምቹ ለማድረግ የቦታዎቹ ጠቋሚ መረጃዎች እየተሰበሰበ መሆኑንም ገልጸዋል። በተጨማሪም ተጓዦቹ በጉብኝታቸው ወቅት ደህንነታቸው እንዲጠበቅና ምቾት እንዲሰማቸው በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ቱሪዝምን በማሳደግ የዘፉን አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማሳደግ የሚሰራው አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም