ቀጥታ፡

የሰሊጥን ምርታማነት ለማሳደግ ክልሉ ድጋፍ ያደርጋል---ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

መቀሌ ሰኔ 4/2010 የሰሊጥን ምርታማነት በጥራት ለማሳደግ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሃገር አቀፍ የሰሊጥ ቢዝነስ ፎረም ትናንት ሲጠናቀቅ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሉት፣ከቡና ቀጥሎ ኢትዮጵያ ከፍተኛው የውጭ ምንዛሬ ገቢ የምታገኝበት የሰሊጥ ምርት ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል። "የሰሊጥ ምርትን በዓለም ገበያ በመጠን፣በዓይነትና በጥራት እንዲቀርብ የክልሉ መንግስት በአሰራርና፣በህግ ማእቀፍና በሌሎች ዘርፎች ልዩ ድጋፍ ያደርጋል "ብለዋል። የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል ተስፋ ካላቸው የግብርና ምርቶች መካከል ሰሊጥ አንዱ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን፣ምርቱ የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ እሴት  ጨምሮ ወደ ዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚገባ አመልክተዋል። " ምርቱን በተለመደው የግብይት ስርዓት ወደ ገበያ ማቅረብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣በዘርፉ ላይ የሚታዩ የገንዘብ ብድር አቅርቦትና  ውስብስብ የግብይት አሰራር ችግሮች በተቋማዊ አሰራር ለመፍታት የክልሉ መንግስት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል። የፌደራል መንግስታት የፋይናንስ ተቋማት፣የምርምር ማዕከላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሰሊጥ ምርትን በጥራት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታሁን ናና በበኩላቸው በፋይናንስ ተቋማት ላይ የቀረቡ ጥያቄዎችን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ባንኮች ያላቸው ውስን ሃብት ለብድር ፈላጊዎችና ጠያቂዎች መስጠት የሚችሉት የሰጡትን ብድር በአግባቡ መመለስ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል። " የሃገራችን አብዛኛዎቹ ባለሃብቶች ብድር መውሰድ እንጂ የመመለስ መልካም ልምድ ስለሌላቸው ባንኮች የሚጠየቁትን የገንዘብ  ብድር መስጠት እየተቸገሩ ይገኛሉ" ብለዋል። አቶ ጌታሁን ልማት ባንካቸው የሰጠውን ብድር ጠቅሰው እንዳሉት፣በሰሊጥና በሌሎችም ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሃብቶች በሰባት ዓመታት ውስጥ በብድር ከሰጠው ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ እስካሁን የተመለሰው 2 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። ባለሃብቶች፣ባንኮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ከቻሉ ችግሩን በሂደት እንደሚፈታና ባንካቸው ለሚጠየቀው የብድር ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። በፎረሙ የተሳተፉት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባወጡት የአቋም መግለጫ ፣ለምርቱ ማደግ ማነቆ የሆኑ የፋይናንስ አቅርቦትና የአሰራር ውጣውረዶችን ለማስወገድ በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጧል። በተለይ ዘርፉን ለማሳደግ የሚጠይቀውን መዋእለ-ንዋይ ከፋይናንስ ተቋማት ለማግኘት ያለው ውጣውረድ እንዲስተካከል ከሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል መንግስታት ጋር ትስስር እንደሚፈጥሩ ነው በአቋም መግለጫቸው ያመላከቱት። በፎረሙ ምሁራን፣የምርምር ማዕከላትና የባንክ የስራ ኃላፊዎች፣የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎች አምራች ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም