ብልሹ አሰራሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በእውቀት የተገነባ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ---ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
ብልሹ አሰራሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በእውቀት የተገነባ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ---ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዳማ ኢዜአ ሐምሌ13/2011 በየደረጃው የመንግስት መዋቅሮች ብልሹ አሰራሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በዕውቀት የተገነባ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ። የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ለዘጠነኛ ጊዜ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 200 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። በክብር እንግድነት የተገኙት ዶክተር ግርማ አመንቴ በምረቃው ስነሰርዓት ወቅት እንዳሉት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማሻሻልና በየደረጃው የመንግስት መዋቅራዊ አስተዳደር ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት መረባረብ ወሳኝ ነው ። "ተቋሙ ከክልሉ የተሰጠውን ልዩ ተልዕኮ ይዞ ለውጡን ለማሳካት በሚወጡ ፖሊዎች፣ ስትራቴጂና አሰራሮች ላይ ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል "ብለዋል። የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በዕውቀት የበቃ አስፈፃሚ ኃይል መገንባት ሲቻል በመሆኑ በህጎች ፣ አሰራሮችና ስትራቴጂዎች ላይ የሚታውን የማስፈፀም አቅም ውስንነት ችግር ለማቃለል የተመራቂዎች ሚና የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይም ቀልጣፋና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ተመራቂዎቹ በቆይይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር መተርጎም እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ በበኩላቸው ተቋሙ የክልሉን አመራሮችና የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞችን አቅም ለማብቃት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በ2009 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ያደገው የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ የክልሉ መንግስት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲቀላጠፍ ከ100 በላይ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማከናወን ለተጠቃሚው አካል ማድረሱን አመልክተዋል። ከ260 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክልሉ መንግስት ሲቪል ሰራተኞችንና አመራሮችን አጭርና ረጅም የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል። የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዲፕሎማና በዲግሪ ማስመረቁን ጠቅሰው የዛሬው ተመራቂዎች ለውጡን በዕውቀት ፣ በክህሎትና በጥናትና ምርምር መደገፍ የሚያስችል አቅም እንዲቀስሙ መደረጉን ገልጸዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል አብዱልጀዋል አህመድ በሰጠው አስተያየት በስልጠና ቆይታው ያገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም ህብረተሰቡ በአገልግሎት ማርካት የሚያስችል አቅም መጨበጡን ተናግሯል ።