ቀጥታ፡

በሶስተኛው ዙር የቦክስ ክለቦች ውድድር አዲስ አበባ ፖሊስና ማራቶን አሸነፉ

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 በሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ በወንዶች ማራቶን አጠቃላይ አሸናፊ ሆነዋል። ከግንቦት 30 ቀን 2010  ጀምሮ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ውድድር ትናትን ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተውጣጡ 80 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ክለቦች እንዲሁም ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ጎንደር ከነማና የሶማሌ ክልል የቦክስ ቡድኖች በውድድሩ የተሳተፉ ክለቦች ናቸው። የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ለአራት ቀናት በተካሄደው ውድድር በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ፤ በወንዶች ማራቶን አጠቃላይ አሸናፊ ሆነዋል። ሁለቱ ቡድኖች የውድድሩ አሸናፊ በመሆናቸው የዋንጫ ሽልማት እንዳገኙም ገልጸዋል። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደቶች ውድድሮች ተካሂደዋል። በአጠቃላይ በሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር 13 የፍጻሜ ውድድሮች እንደተካሄዱና በየክብደት ዘርፉ ላሸነፉት የወርቅ እንዲሁም ሁለተኛና ሶስተኛ ለወጡት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል። ተተኪ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ እንደነበርም አመልክተዋል። ውድድሩ የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ካካሄዳቸው ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሶስተኛው እንደሆነና የመጀመሪያና የሁለተኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድሮች በአዲስ አበባና በሆሳዕና ከተማ መካሄዱን አስታውሰዋል። የመጨረሻው የክለቦቹ ውድድር ሰኔ መጨረሻ 2010  በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል። በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ተደምሮ የ2010  የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም