የትምህርት ተቋማት አመራሮች የኢትዮጵያውያን የቀደመ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብት መስራት ይጠበቅባቸዋል---ሙስጠፌ መሐመድ

72
ባህርዳር ኢዜአ ሐምሌ 13/2011 በትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያሉ አመራሮች የኢትዮጵያ የቀደመ የህዝቦች የመቻቻልና የመከባባር እሴቶች እንዲጎለብቱ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ተናገሩ። የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ  በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 9 ሺህ 750 ተማሪዎችን ዛሬ  አስመርቋል፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ሙስጠፌ  እንዳሉት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ትልቁ ችግር የትምህርትና ስልጠና ተቋማት  የመቻቻልና የመከባባር እሴቶች መቀጠል ላይ  የሚያከናውኑት ስራ በመሸርሸሩ ነው። ትምህርት የአንድን ሃገር እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን ብቸኛ ቁልፍ መሳሪያ ቢሆንም የትምህርት ተቋማት የህዝቦችን የጋራ እሴቶች በማስቀጠል በኩል ክፍተቶች ተስተውሎባቸዋል፡፡ እሳቸው እንዳመለከቱት እንደ ሃገር በትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያሉ አመራሮች የኢትዮጵያ የቀደመ የህዝቦች የመቻቻልና የመከባባር እሴቶች እንዲጎለብቱ እንደ ዜጋ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ጥሩውን ነገር በማስቀጠልና መጥፎውን በማረም ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠንክሮ እንዲቀጥል መስራት አለባቸው። እውቀት የሚለካው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅሎ በሚሰራው ስራ በመሆኑ ተማሪዎችም እስካሁን ያገኙትን እውቀት ህዝቡን አንድ በሚያደርግና  የተሳሳቱ አካሄዶች  እንዲታርሙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የነበረ የታላቅነትና የስልጣኔ ገናናነት በአጭር ጊዜ በተማሩ ልጆቿ ሊመለስ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑንም አቶ ሙስጠፌ አብራርተዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ተመራቂዎች በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመመራት እንደ አዲስ እየተገነባች ያላችው ኢትዮጵያን በማሳደግ በኩል ርብርብ እንዲያርጉ አሳስበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪው በግልም ሆነ በመንግስት ስራ ሲሰማሩ በኢትዮጵያዊነት ወኔ እና በመቻቻል መንፈስ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡ ዩኒቨርስቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ  ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቁ ናቸው፡፡ ከመካከላቸውም ከሁለት ሺህ 600 በላይ  ሴቶች ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ ባደረጉት  አስተዋጽኦ  ለዶክተር ሰገነት ቀለሙ፣  ለስዊድናዊው ፕሮፌሰር ሀንስ ማትሰን እና ለአሜሪካዊው ማርክ ጌልፋንድ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ  የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌውን ጨምሮ ሌሎችም የክብር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም