ቅዱስ ጊዮርጊስ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር አይሳተፍም - ኢዜአ አማርኛ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር አይሳተፍም
አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በ43ኛው የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር እንደማይሳተፍ አስታወቀ። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር ዘንድሮ በታንዛንያ ዳሬሰላም ከሰኔ 22 እስከ ሐምሌ ሰባት ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምኒልክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ክለቡ በታንዛንያ በሚደረገው የሴካፋ ክለቦች ውድድር አይሳተፍም። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና በጥሎ ማለፍ ባለበት ጨዋታ እንዲሁም በሐምሌ 2010 ዓ.ም ወደ ኔዘርላንድስ በመጓዝ ከቪቪቪ ቬንሎ ክለብ ጋር በሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ምክንያት በሴካፋው ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ ገልጸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ ባለመሳተፉ በሴካፋ ውድድር የሚሳተፉ ቡድኖች ቁጥር ወደ 11 ዝቅ ብሏል። ሚያዚያ 2010 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ አሳውቆ ነበር። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር በበጀት እጥረት ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት አለመካሄዱ ይታወቃል። ውድድሩ ከመቋረጡ በፊት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2015 በታንዛንያ ሲካሄድ የአዘጋጇ አገር ክለብ አዛም የኬንያውን ጎር ማሂሃ ሁለት ለዜሮ በመርታት አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1974 የተጀመረ ሲሆን የታንዛንኒያው ሲምባ ክለብ ስድስት ጊዜ የውድድሩን ዋንጫ ሲያነሳ፤ የኬንያዎቹ ኤኤፍሲ ሊኦፓርድ፣ ጎር ማሂሃና ቱስከር እንዲሁም የታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ አምስት ጊዜ አሸንፈዋል። በምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ውድድር ታሪክ ሻምፒዮን የሆነ የኢትዮጵያ ክለብ የለም። ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2010 በውድድሩ ፍጻሜ የደረሰበትና በ2011 አራተኛ የወጣበት በኢትዮጵያ ክለቦች የሴካፋ ውድድር ታሪክ ትልቁ የሚባል ውጤት ነው።