በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 24 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 24 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
መቐለ ኢዜአ 11/11/2011 የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈናቅለው በትግራይ ክልል ለሚገኙ ወገኖች ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ እንደገለፁት ድጋፉ የተለያዩ አልባሳት ፣ ዘይት ፣ ስኳር የመሳሰሉ ቁሳቁስን ያከካተተ ነው ። ድጋፉ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን በቅርቡም በተመሳሳይ ሁኔታ 18 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል ። የትግራይ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል የገቢዎች ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባባር ለሰጡት ድጋፍ በተፈናቃዮቹና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ111ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ መንግስት ተፈናቃዮቹን በዛለቂነት ለማቋቋም ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ከተፈናቃዮቹ መካከል አቶ ሚዛን ሃይላይ እንደገለጹት ጉምሩክ ኮሚሽን የችግራቸው ተካፋይ መሆኑ ለሌሎች በአርአያነት እንዲታይ የሚያደርገው መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ሙሉዓለም መንግስተአብ የተባሉ ተፈናቃይ በበኩላቸው "መንግስት ከጊዜያዊ እርዳታው ባሻገር በዘላቂነት ተቋቁመን ከተረጂነት እንድንወጣ ሊያግዘን ይገባል" ብለዋል ። የገቢዎች ሚኒስቴር ከእዚህ ቀደም በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል።