ጋዜጠኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ዘገባ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጋዜጠኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ዘገባ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ትክክለኛ መረጃንና እውቀትን መሰረት ያደረገ ዘገባ እንዲያቀርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ። ሚኒስቴሩ “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና የሚዲያ ሚና “ በሚል ርዕስ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ያዘጋጀው የሁለት ቀናት ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል። የስልጠናው ዓላማ ጋዜጠኞች የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ብሄራዊ ጥቅም አውቀው ዘገባ እንዲያዘጋጁ የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር ነው። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የሚዲያ ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በተገቢ ጊዜ እና በበቂ ትንታኔ በመዘገብ በሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት የፖሊሲ አቀራረጽና የገጽታ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት ይገባቸዋል። ስልጠናው ጋዜጠኞች የውጭ ግንኙነት እውቀታቸውን ከፍ በማድረግ ሙያቸውን በጥራት እንዲያከናውኑ እገዛ እንደሚያደርግ የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴሩ የውጭ አገልግሎት ስልጠና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ናቸው። ዶክተር ማርቆስ እንደሚሉት "የውጭ ግንኙነት ሥራ ከተለያዩ ሀገራዊ ሚስጥራዊ ጉዳዮች ጋር ጭምር የተያያዘ በመሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎችን የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ ይሻል።" በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምሁራን አማካኝነት የሚሰጠው ስልጠና ኢትዮጵያ ከጎረቤትና መካከለኛ ምስራቅ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት እንደዚሁም በአካባቢው በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ለተሳታፊዎች ጠቃሚ ግንዛቤ ያስጨብጣል ተብሏል። ከተለያዩ አካላት የሚለቀቁ ትክክለኛ ያልሆኑ ዜናዎችን የመለየትና የመከላከል ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚያግዛቸው መሆኑም ተመልክቷል።