በኢትዮጵያ ሐምሌ 22 ቀን ለሚተከሉት ችግኞች የዝግጅት ስራ እየተገባደደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሐምሌ 22 ቀን ለሚተከሉት ችግኞች የዝግጅት ስራ እየተገባደደ ነው
ሐምሌ 11/2011 በኢትዮጵያ በሓምሌ 22 ቀን ለሚተከሉት 200 ሚሊዮን ችግኞች የዝግጅት ሥራው እያተገባደደ መሆኑን በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው የክረምት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ። የቴክኒክ ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳሉ ተብሏል። መርኃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ያስጀመሩት የዘንድሮ የክረምት የአራት ቢሊዮን የችግኝ ተከላ አካል መሆኑም ተጠቁሟል። በየአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ልማት አስተባባሪና የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ተፈራ መንግሥቴ እንደተናገሩት፤ መርኃ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን የዝግጅት ሥራዎች እየተገባደዱ ናቸው። በቅድሚያም የችግኝ ተከላ ስፍራዎችን የመከለል 450 ሥፍራዎችን በተለያዩ የአገሪቷ አከባቢዎች መለየታቸውን ነው የጠቆሙት። ከዚህ ጎን ለጎንም የሚተከሉ ችግኞች በየስፋራው የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱንና የጉድጓድ ቁፋሮም በተሳካ መልኩ መካሄዱን ነው የጠቀሱት። እስካሁንም ለችግኞቹ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ጉድጓዶች መቆፈራቸው ተጠቁሟል። ሐምሌ 22 ቀን የሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ከጠዋቱ 12 ሠዓት እስከ ምሽት 12 ሠዓት እንደሚሆን ነው ያስታወቁት። በዚህም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸው፤ ይህንን ሥራ የሚያስተባብሩትም ከመካከላቸው እየተመረጠ መሆኑን ተናግረዋል። ጎን ለጎንም የግል ተቋማት ሠራተኞች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አርሶ አደሩን ጨምሮ በዚሁ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። ይህንንም የማሰተባበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆም። በግብርና ሚኒስቴር የዘር ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው፤ የሚተከለው ችግኞች የተራቆተው አከባቢ እንዲያገግምና ሥነ-ምህዳሩ እንዲስተካከል ይጠቅማል። በዚህም መሰረት የሚተከሉት ችግኞች የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የተለያዩ የእጽዋት ዓይነት መሆናቸውን ነው የገለጹት። ለአብነትም ችግኞች ለፍራፍሬ፣ ለውበት፣ ለእንሰሳት መኖና ለአፈርና ለውኃ ጥበቃ አገልግሎት እንደሚውሉ በመጠቆም። በተቻለ መጠንም ከአከባቢው ሥነ-ምህዳር ጋር ተቃራራቢ የሚሆኑ ችግኞች መደልደላቸውን ጠቁመው፤ በመጓጓዝ ምክንያት የሚደርሱ ችግሮችና ለማቃለል ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ እንዴት እንደሚከናወን መንግሥት ከዚህ በኋላ አቅጣጫ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ ችግኝ እንዲተክል ጥሪ አስተላልፈዋል። በሐምሌ 22 ቀን የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር 38 ሚሊዮን የሚሆነው በከተሞች አካባቢ የሚካሄድ ሲሆን፤ የከተማ ነዋሪዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል። በተለይም አቅሙ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች ችግኞችን ችግኝ ከሚፈላባቸው ሥፍራዎች በመግዛት ያላቸውን አጋርነት እንዲያሳዩ ነው የተጠቆመው። ነገር ግን አቅም የሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የከተማ አስተዳደሮች የሚያቀርቡትን እንዲጠቀሙ ጠቁመዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት አስካሁን በአንድ ጀምበር 65 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ህንድ ቀዳሚ አገር ነች። በመጪው ሐምሌ 22 ቀን በሚካሄደው የ200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላን በማሳካት ደግሞ ኢትዮጵያ የአንደኝነት ደረጃዋን ከህንድ ለመቀበል እንደምትችል ነው ዶክተር ተፈራ የገለጹት። በእስካሁኑ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በመላ አገሪቷ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአገሪቷ የአረንጓዴ ሽፋን 15 በመቶ መሆኑን ተገልጿል።