የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ የወደቡን ስራ እያቀላጠፈው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ የወደቡን ስራ እያቀላጠፈው ነው
ሐምሌ 11/2011 ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ የተዘረጋው የምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ቀልጣፋ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እያገዘ መሆኑ ተገለፀ። የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት ከ250 እስከ 500 ኮንቴነሮች ከጅቡቲ ወደብ በደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ይጓጓዙ ነበር። ኮንቴነሮቹን ለማጓጓዝም ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ይሰማሩ ነበር። የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ግን በ112 የጭነት መኪናዎች ይጓጓዙ የነበሩትን ኮንቴነሮች በአንድ ቀን በባቡር ማጓጓዝ እንደተቻለ ሞጆ ደረቅ ወደብ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሚደቅሳ በስፍራው ለተገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ገልፀዋል። የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመር ቀደም ሲል በደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ይስተዋል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ እንዳስቀረውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። እንዲሁም በተሽከርካሪ እስከ ሶስት ቀን ይፈጅ የነበረው ጉዞ ከስምንት እስከ 12 ሰዓት እንዲያጥር ማድረጉንና የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ ረገድም ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር ኮንቴነሮችን በተሽከርካሪዎች የማጓጓዙ ሂደት የሚወሰደውን ረጅም ጊዜ በማሳጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል። የሞጆ ደረቅ ወደብ የባዶ ኮንቴነር አፐሬሽን ቡድን መሪ አቶ ታሪኩ ገብረሥላሴ በበኩላቸው ባቡሩ ከጅቡቲ ወደብ በኮንቴነሮች የሚጓጓዙትን የገቢ ዕቃዎች ወደ ደረቅ ወደቡ ካደረሰ በኋላ የወጪ ንግድ ምርቶች ካሉ ይዞ እንደሚመለስም አስረድተዋል። ወደጅቡቲ ወደብ የሚጓጓዙ የወጪ ንግድ ምርቶች ከሌሉ ደግሞ ባዶ ኮንቴነሮችን ይዞ በመመለስ የአገሪቱ የወጭና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል። በሞጆ ደረቅ ወደብ የሚከናወነውን የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ የበለጠ ለማሳለጥ ደረቅ ወደቡ ከዋናው የባቡር መስመር ወደሶስት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የባቡር ሀዲድ መስመር በራሱ ወጪ ወደቅጥር ጊቢው መዘርጋቱን አቶ ደረጃ አስታውቀዋል። ወደቅጥር ጊቢው የተዘረጋው የባቡር ሀዲድ መስመር በደረቅ ወደብ ጊቢው ውስጥ ከገባ በኋላ በአራት መስመሮች ተከፋፍሎ መዘርጋቱንም ገልጸዋል። ከተቋቋመ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው የሞጆ ደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ተገቢው የመሰረተ ልማት አውታር ሳይሟላለት ነበር። ሥራውን የጀመረውም በሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ላይ በተለምዶ ገረጋንቲ በመባል የሚታወቀውን ቀይ ጠጠር በማፍሰስ ነበር ያሉት አቶ ደረጀ፤ የፍተሻ ሥራውም የሚከናወነው በድንኳን ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም ደርቅ ወደቡን የማስፋፋቱ ሥራ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ደረቅ ወደቡ በጠቅላላው በ62 ሄክታር መሬት በሚሸፍን ቦታ ላይ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ወደፊትም ተጨማሪ ማስፋፊያ ለማከናወን የሚያስችል 82 ሄክታር መሬት እንዳለው ከዳይሬከተሩ ማብራሪያ ማወቅ ተችሏል።