የመላው አማራ የባህል ስፖርት ውድድር በምእራብ ጎጃም አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

64
ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 22/2010 በሰሜን ሽዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ከተማ የተካሄደው 15ኛው የመላው አማራ የባህል ስፖርት ውድድር በምእራብ ጎጃም ዞን አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በክልሉ ዞኖች መካከል ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የሰነበተው ውድድር ምእራብ ጎጃም በ49 ነጥብ፣የአዊ ብሔረሰብ ዞን በ44 ነጥብ እና የደቡብ ጎንደር ዞን 29 ነጥብ በማግኘት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። አዘጋጁ የሰሜን ሸዋ ዞን 22 ነጥብ በማግኘት በስድስተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችሏል። በባህላዊ ስፖርት ውድድሩ ከ600 በላይ ስፖርተኞች በፈረስ ጉግስና ሸርጥ፣ ትግል፣ ገና ጫወታን ጨምሮ በ10 ባህላዊ ስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል። የአማራ ክልል የባህል ስፖርቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዓለም ሁነኛው ለአሸናፊዎች ዋንጫና የምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ እንደገለፁት በውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው 16ኛው የባህል ስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ውድድር ክልሉን የሚወክሉ 80 ተተኪ ስፖርተኞች ተመልምለዋል። ከደቡብ ወሎ ዞን ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ዘሩ ጋሻው እንደገለፀው ውድድሩ እርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከሩም በላይ ለባህል እድገት እና መስፋፋት ከፍተኛ ትርጉም አለው። ከሚያዚያ 14 እስከ 21 2010 ዓ.ም በተካሄደው ውድድር ከ10 ዞኖች የተውጣጡ ከ600 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም