ቀጥታ፡

የችግኝ የመጽደቅ መጠንን መከታተል የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር ተዘጋጀ

ሐምሌ 11/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሚተከሉት ችግኞች በአግባቡ መጽደቃቸውን ለመከታተልና ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱን የክረምት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ። በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው የክረምት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ በመጪው ሃምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሚተከለውን የ200 ሚሊዮን ችግኝ ዝግጅት አስመልክቶ  ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በዘመቻ መልክ የችግኝ ተከላ ተግባራት የሚከናወኑ ቢሆንም ፀድቀው ወደዛፍነት ይለሙ ዘንድ የሚደረገው ክትትልና ክብካቤ አነስተኛ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እያመጡ አለመሆኑ ይነገራል። በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው የክረምት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይም በመግለጫው ላይ ያመለከቱት ይህንኑ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ በተለያየ ወቅት ችግኞች የተተከሉ ቢሆንም ያሉበትን ደረጃ በመከታተል በኩል ውስንነቶች አሉ። ከአሁን በኋላ ግን ይህ ችግር ይቀረፋል፤ በዚህ ዓመት በመላው አገሪቱ ለመትከል የታሰበው 4 ቢሊዮን ችግኝም ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ የሚገኝበት ደረጃን መከታተል የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተዘርግቷል ሲሉ ነው ዶክተር ሰለሞን ያስታወቁት። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት  የተተከለውን ችግኝ መጽደቅ አለመጽደቁን ለመከታተል የሚያስችል አገር አቀፍ ድረ-ገጽና ጂፒኤስ አዘጋጅቷልም ብለዋል። ቴክኖሎጂው የተተከሉ ችግኞች ዓይነትን ጨምሮ አጠቃላይ የችግኞቹን ሁኔታ የተመለከተ መረጃ የያዘ ሲሆን ያሉበትን የእድገት ደረጃ ቦታው ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ ለማወቅ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ቴክኖሎጂው የተተከሉ ችግኞች የመድረቅና ሌላ ችግር ሲያጋጥማቸው መረጃውን በማየት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል፤ ይህም ችግኞቹ የቅርብ ክትትልና ክብካቤ ተደርጎላቸው በአግባቡ እንዲፀድቁ ያግዛል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ሂደትን የተመለከተ መረጃ ከወዲሁ የሚሰበሰብ ሲሆን ከጂፒኤስ በመነሳትም ካርታ እንደሚዘጋጅ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በመጪው ሃምሌ 22 ቀን 2011 ዓም የሚተከሉ ችግኞችን ጨምሮ ሁሉም ችግኞች ወደመረጃ  ቋቱ እንደሚገቡም ተገልጿል። ኢትዮጵያ ወደፊት የራሷ ሳተላይት ሲኖራት ደግሞ ደንን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብና በባለሙያዎች በማስተንተን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል ብለዋል። የችግኝ መርሃ ገብሩን ለማሳካት በአሁኑ ወቅት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እና 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ እንደተዘጋጀ ተገልጿል። መርሃ ግብሩ በይፋ ከተጀመረበት ካለፈው ወር ጀምሮም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ በመላው አገሪቱ ተተክሏል። በችግኝ ተከላው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በስፋት እንዲሳተፍ በመግለጫው ላይ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም