ቀጥታ፡

ፍርድ ቤቱ በአቶ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ያልተያዙ ስድስት ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ሰጠ

ሐምሌ 11/2011 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በአቶ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ያልተያዙ ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ሰጠ። በ2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው እጃቸው ያልተያዘ ስድስት ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 7ኛ ተካሳሽ አብዲ ጀማል አህመድ፣ 11ኛ ተከሳሽ ኡመር መሐመድ፣ 24 ተከሳሽ አብዱረዛቅ ኤልሚ፣ 26ኛ ተከሳሽ መሐመድ አህመድ ኑር (በቅጽል ስም መሐመድ ሄሪዬ)፣ 31ኛ ተከሳሽ ሀሰን ሁሴን እና 32ኛ ተከሳሽ ሙሳ አረብ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ተከሳሾች ናቸው። በእነ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 49 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ስድስቱን ተከሳሾች ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዲያቀርብ ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በአድራሻቸው ፈልጎ ማቅረብ አለመቻሉን ለችሎቱ ያስረዳ ሲሆን ዐቃቤ ህግም ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲቀርቡ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ተከሳሾቹ በጋዜጣ ማስታወቂያ እንዲጠሩ ችሎቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወቃል። ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠርጣሪዎቹ ለዛሬ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ጥሪ ተደርጎላቸው አለመቅረባቸውን ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ አስረድቷል። ተጠርጣሪዎቹ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ከሆኑ ከ12 ዓመት በላይ የሚያስቀጣቸው መሆኑን የገለጸው ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው በሌሉበት መታየቱ አግባብ ስለሆነ የተመሰረተባቸው ክስ በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተመሳሳይ በዚሁ የክስ መዝገብ ካልተያዙት ተከሳሾች መካከል ሙሴ እድሪስ፣ መሐመድ አህመድ ኑር፣ ጄነራል አብራህማን አብዱላሂ፣ ኑረዲን አብዱላሂ እና ሻለቃ ሼክ መሐመድ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደማይገኙ ፖሊስ በማስረጃ ማረጋገጡን ለችሎቱ አመልክቷል። ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ፖሊስ የጠየቀ ሲሆን እጃቸው ያልተያዘ ሌሎች 23 ተከሳሾችን ፈልጎ ለማቅረብ ደግሞ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው አመልክቷል። ዐቃቤ ህግ በበኩሉ በአድራሻቸው ተፈልገው ያልተገኙት አምስቱ ተካሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው፤ ሌሎች ያልተያዙ 23 ተከሳሾች ፖሊስ ለጠየቀው ተለዋጭ ቀጠሮ ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ወይም እስከ አሁን የነበረው ሂደት በቂ ነው ብሎ ካመነ ተከሳሾቹ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲቀርቡ ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ፖሊስና ዐቃቤ ህግ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በተጨማሪም ችሎቱ በእነ አቶ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ህግን ክርክር ሰምቶ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ እንደነበር ገልጿል። ነገር ግን ጉዳዩን ከሚከታተሉት ዳኞች መካከል አንድ ዳኛ በእክል ምክንያት ባለመኖራቸው ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ዛሬ ብይን መስጠት አለመቻሉን የገለጸው ችሎቱ እክል የገጠማቸው ዳኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚመለሱና በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም