በመዲናዋ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የገደበው መመሪያ ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የገደበው መመሪያ ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም ተባለ
ሐምሌ 11/2011 የአዲስ አበባ አስተዳደር በቅርቡ የተገበረው የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በሠዓት የሚገድበው መመሪያ የመዲናዋን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እንደሆነ የዘርፉ ተዋንያን አመለከቱ። የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ መመሪያው ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተወሰደ፣ ተገቢና መለመድ ያለበት ነው ብሏል። የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት በመቆጣጠር ብሎም የተሽከርካሪ አደጋን ለመከላከልና የኢኮኖሚ ብክነትን ለመቀነስ የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በሠዓት የሚገድብ መመሪያ ተተግብሯል። መመሪያው ማናቸውም ቀላል ተሽከርካሪዎች ከማለዳው 12፡30 እስከ ረፋዱ 4፡00 ሠዓት እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ10፡00 እስከ ምሽቱ 2:00 ሠዓት ወደ መዲናይቱ እንዳይገቡ፣ እንዳይወጡና ጭነት እንዳያራግፉ ይከለክላል። በተመሳሳይ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከማለዳው 12፡30 እስከ ምሽቱ 2:00 ሠዓት ወደ መዲናዋ መግባትና መውጣትም ሆነ ጭነት ማራገፍና መጫን እንደማይችሉ ደንግጓል። የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ በመመሪያው አፈጻጸም ላይ የሚታዩ እውነታዎችን አስመልክቶ ዛሬ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተዋንያን ጋር ተወያይቷል። በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ጋይሞ ይብራህ መመሪያው የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታና የሚያስከትለውንም ችግር ያገናዘበ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ተሽከርካሪዎች ጅቡቲ ለመድረስ በመዘግየታቸው በወደቡ ላይ የሚከማቸው እቃ መጠን እንደሚጨምርና ለሚቆይበት ጊዜም ተጨማሪ ዶላር እያስወጣ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ተወካይ አቶ ግዛት ወርቁ ደግሞ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጣው ቡና ተበጥሮ ወደ ወደብ የሚላከው ከአዲስ አበባ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የጭነት ተሽከርካሪዎች በቀን ተንቀሳቅሰው መስራት ባለመቻላቸው ምሽቱ ሲጠበቅ ጅቡቲ ወደብ ላይ መርከብ ቆሞ ስለማይጠብቅ 'ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ያመዝናል' ብለዋል። መመሪያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በአንድ ሳምንት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ወደ ውጭ የሚላከው ቡና በግማሽ እንደቀነሰም ተገልጿል። በኮንስትራክሽን ዘርፍም በቀን ብቻ የሚሰሩና በምሽት ለመስራት በህግ የተከለከሉ ግንባታዎች በመኖራቸው ዘርፉን ወደኋላ እንዳይጎትተው ስጋታቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የአውቶ ሴፍቲ ሬዲዮ ፕሮግራም ተወካይ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ የመመሪያው መውጣት 'ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ ነው' ሲሉ ተናግረዋል። መመሪያው በመተግበሩ ትላልቅ ማሽኖችን ከጫኑ ተሽከርካሪዎች ጋር የሚጋፉ ህጻናትን የሚያጓጉዙ ሚኒባሶች ጫናና በመንገድ መዘጋጋት ከስራ የሚዘገዩ ሰራተኞች እንግልት 'ቀንሷል' ብለዋል። የአፈጻጸም ውስንነት መኖሩን ግን አልሸሸጉም። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃለፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የተለያዩ አማራጮችን የመጠቀም ልምዳችን አናሳ ስለሆነ እንጂ መመሪያው 'ችግር የለበትም' ነው ያሉት። ከጉምሩክ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ የአፈጻጸም ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት የመፍትሄ ሃሳብ ቀርቦ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በኮንስትራክሽን፣ በቡና ማጣራት ሂደትና በወተት ማቀነባበር ተግባራት የሚስተዋለው መዘግየትና ኪሳራ ሌሎች አማራጮችን ካለመጠቀም የመነጨ ችግር እንደሆነም ተናግረዋል። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ሌሎች አገሮች ቀንና ምሽትን በፈረቃ የመስራት ልምድ ቢኖር ችግሩ ጉልቶ አይታይም ነበር ብለዋል። በመሆኑም በፈረቃ የመስራት ባህላችንን በማሳደግ መመሪያውን አክብሮ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መመሪያው ከህንድ አገር በመጡ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን ችግሮች ካሉበትም 'እያየን ማስተካከያ እናደርጋለን' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከከተማ አስተዳደሩ የበላይ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ልዩ ፈቃድ የሚሰጣቸው ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል። ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 4፡00 ሠዓት እስከ ቀኑ 10:00 ሠዓት ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች፣ ህጋዊ የድንገተኛ አደጋ መከላከል ስራ የሚያከናውኑ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች በመመሪያው አይካተቱም።