ማህበሩ የገዛቸውን 11 ተሽከርካሪዎች ለሀድያ ዞን አስተዳደር አስረከበ

59
ሆሳዕና ሐምሌ 10/2011 (ኢዜአ)  የሀድያ ልማት ማህበር ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከቀረጥ ነጻ ገዝቶ ያስገባቸውን 11 ተሽከርካሪዎች ዛሬ ለዞኑ አስተዳደር አስረከበ። በርክክብ ስነ ስርዓቱ ወቅት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ዝና እንዳሉት ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመቆም የልማት እቅዶች እንዲሳኩ እያገዘ ነው። ማህበሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ዛሬ ለዞኑ ያስረከባቸው ተሽከርካሪዎች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ለመስራት እንቅፋት የነበረውን የተሽከርካሪ እጥረት ችግር  እንደሚያቃልል ገልጸዋል። በአግባቡ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውሉም አሳስበዋል። የልማት ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ታረቀኝ በበኩላቸው ልማት ማህበሩ  ያደረገው ድጋፍ የዞኑ አስተዳደር ለተሽከርካሪ ግዥ የሚያውለውን በጀት ለልማት ስራ በማድረግ ለልማት እቅዶች መሳካት እንደሚረዳ ተናግረዋል። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላ አቦ ልማት ማህበሩ "በዞኑ በመንግስት የማይሸፈኑ የልማት ስራወዎች  ከአስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል " ብ ለዋል። ልማት ማህበሩ በትምህርት መስክ ጥራትን ለማምጣት በመንግስት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ከማገዝ አንጻር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ  በጀት በመመደብ አዳሪ ትምህርት ቤት እያስገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሀድያን ባህል ፣ታሪክና ቅርስ በማጥናት ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃና ፣በግብርና ልማት ዙሪያም እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ልማት ማህበሩን በማጠናከር ከአባላት፣ ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጪ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዞኑ ልማት መፋጠን ድጋፉን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ማህበሩ ከ14 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ገዝቶ ለዞኑ አስተዳደር ያስረከባቸው  11 ተሽከርካሪዎች ከአባላቱና ሌሎች ደጋፊዎቹ ባገኘው ድጋፍ እንደሆነ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም