ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመቐለ ከተማና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010  በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም መቐለ ከተማ ከፋሲል ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ ተጠናቋል። በ26ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል በሰበታ ስታዲየም ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰአት የመቐለ ከተማና ፋሲል ከተማ ጨዋታ እንዲካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም፤ በዝናብ ምክንያት በክለቦቹ ጥያቄ መሰረት በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተደርጓል። በዚሁ መሰረት ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል። መቐለ ከተማ ዛሬ ያገኘውን አንድ ነጥብ ተከትሎ ሌሎቹ ቡድኖች ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ በ43 ነጥብ ሊጉን በድጋሚ መምራት ችሏል። የ26ኛ ሳምንት የሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከሃዋሳ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዲያ ከተማ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በክልል ከተሞች በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ፣ በአርባ ምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻና በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከደደቢት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከጅማ አባጅፋር ከቀኑ 10 ሰዓት እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ከተማ በ43 ነጥብ ሲመራ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 42 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አርባ ምንጭ ከተማ፣ ኢትዮ-ኤሌትሪክና ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ16 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ11 እንዲሁም የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በ10 ግቦች ይከተላሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም