ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላው በንቃት እንዲሳተፍ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላው በንቃት እንዲሳተፍ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ
መቱ ኢዜአ ሀምሌ 10/2011 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተነሳሽነት በዘንድሮው ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኝ እንዲተከል የተነደፈውን እቅድ እንዲሳካ ህብረተሰቡ በዘርፉ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ። ከሀገሪቱ የእምነት ተቋማት የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶችና አባላት ከትናንት በስቲያ በአጋሮ ከተማ ከ10 ሺህ በላይ ችግኝ ተክለዋል። በችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ወቅት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት ህብረተሰቡ የዛፍ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት ያለውን ጠቀሜታ በአግባቡ ሊገነዘብ ይገባል። ” ችግኝ ተክሎ መንከባከብና ሰላምን መጠበቅ አንድ ናቸው፤ ስራዎቹ የአሁን ድካማችን ሳይሆን የወደፊት ፍሬያቸው ለሀገር እድገትና ልማት የሚያበረክቱትን ፋይዳ ተገንዝበን በስፋት ልንሳተፍበት ይገባል"ብለዋል። የጅማ ዞን የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ፀሐፊ ፓስተር ሰሎሞን በልሁ በበኩላቸው የኃይማኖት መሪዎች በጋራ ችግኞችን እንደተከሉ ሁሉ ህብረተሰቡም አርአያነታቸውን እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል። ”ሀገራችንን ለማሳደግ በልማቱ መስክ ያለልዩነት በጋራ መረባረብ አለብን ” ሲሉም አክለዋል ። የአጋሮ ከተማ የኃይማኖት አባት ሀጂ ራያ አደም እንዳሉት ደግሞ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ለሀገሪቱ የወደፊት እድገት ወሳኝ በመሆኑ መላው ህዝብ ለእቅዱ ተግባራዊነት እንዲረባረብ ምልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የኃይማኖት አባቶችም የአካባቢ ጥበቃና ችግኝ ተከላ አስፈላጊነት አስመልክተው በህብረተሰቡ ዘንድ ጠንካራ ግንዛቤ ለመፍጠር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ህብረተሰቡ በክረምት ችግኝ ተከላና እንክብካቤ እንዲሳተፍ ያስተላለፉት መልዕክት የሚደገፍ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጎማ ወረዳና አጋሮ ከተማ ቤተ ክህነት ኃላፊ ቄስ መልአከ ገነት ካሴ ናቸው። ”ችግኝ ተክሎ መንከባከብና ልጅ ወልዶ ማሳደግ አንድ ናቸው ” ያሉት ቄስ መላዕከ ገነት ህብረተሰቡ የሚተክላቸውን ችግኞች ልክ እንደአብራኩ ክፋዮች ሊንከባከባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። የኃይማኖት አባቶችና አባላት ችግኞችን የተከሉት በአጋሮ ከተማ ካካሄዱት የአንድ ቀን የሰላምና ልማት ኮንፍረንስ በኋላ ነው ።