በክልሉ ከ400ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሰማሩበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ተመቻቸ

68
መቐለ ሐምሌ10/2011 በትግራይ ክልል ከተያዘው ሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ ከ400ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሰማሩበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ መመቻቸቱ ተገለጸ። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰማሩ ወጣቶች መካከል 35 ሺህ ያህሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ኮሌጆች ተማሪዎች ናቸው። በስራ እንደሚሰማሩ ከሚጠበቁት ወጣቶች መካከል 136 ሺህ ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል። ወጣቶች የሚሰማሩባቸው ስራዎች ተለይተው የተመቻቹ ሲሆን ከስራዎቹ መካከል  ግብርና፣ ትምህርት ፣ጤናው  በተለይ የኤች አይ ቪ/ኤዲስ በሽታ ስርጭትን የመከላከል ስራ እና የደም ልገሳ ይገኙበታል። " በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ላይ የሚሰማራ እያንዳንዱ  ወጣት በሐምሌና ነሐሴ ወራት ውስጥ 72 ሰዓታት እንዲሰሩ መግባባት ላይ መደረሱን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የልማት ተሳትፎ ባለሙያ አቶ የማነ ግርማይ ናቸው። "ወጣቶቹ በአገልግሎት አሰጣጥ ቆይታቸው ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ስራዎች ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል ። በልማት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ከተዘጋጁ ወጣቶች መካከል በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ  ተማሪ አስፋው ይመስገን በሰጠው አስተያየት ለስራው የተነሳሳው ህብረተሰቡን ለማገልገል ካለው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ተናግሯል። "የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ህዝባችን ለማገልገል ብቻ ሳይሆን ወጣቱ ከማህበረሰቡም የስራ ባህልና ግብረገብነትን በተግባር እንዲማር ያግዘዋል "ብሏል። " ህዝባችን ለማገልገል ዝግጁ ነን" ያለችው ደግሞ የዓዲግራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪ ወጣት ሰምሃል አያልነህ ናት። ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከ300 ሺህ በላይ የክልሉ ወጣቶች የተለያዩ ልማት ስራዎች መከናወናቸውም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም