የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ጠቅላላ ምክር ቤት አቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ጠቅላላ ምክር ቤት አቋቋመ
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ጠቅላላ ምክር ቤት አቋቋመ። ጉባኤው ሦስት ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን የቁጥጥር ኮሚቴ ማቋቋም ፣ የአሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋምና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፈደሬሽን ውህደትን የተመለከቱ ናቸው። በጉባዔው በሦስት አባላት ያሉት የቁጥጥር ኮሚቴ ሲቋቋም 25 አባላት ያሉት ጠቅላላ ምክር ቤትም ኮንፌደሬሽኑ አቋቁሟል። ውህደቱን በተመለከተ ክትትል የሚያደርጉ አምስት ሰዎች ከኮንፌደሬሽኑ የቦርድ አባላት መካከል ተመርጠዋል። የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን እንዳሉት ፤ ኮንደሬሽኑን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቁ ሥራ አደረጃጀቱን ማጠናከር ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ የምክር ቤቱና ቁጥጥር ኮሚቴ መቋቋም ለኮንፌዴሬሽኑ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። ለቦርዱ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ማፍለቅ ፣ የሚወርዱ መመሪያዎችን ገቢራዊ ማድረግ ከምክር ቤቱ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል። የምክር ቤቱ አባላት ከአማራ ፣ ከአዲስ አበባ ፣ጥቃቅና አነስተኛና መካከለኛ፣ከሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ፌደሬሽኖች የተውጣቱ ናቸው። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ 100 የሚሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን ያካተተ የምክክር መድረክ በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በምክክር መድረኩ የቻይና ፣ የቱርክ ፣ የህንድ ፣ የጣልያንና የስፔን ኢንቨስተሮች በምክክር መድረኩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ይጠበቃል። ከአገር ውስጥም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአባልነት ይተቀፋሉ ብለዋል። መድረኩ በየሦስት ወሩ በመሰብሰብ በአሰሪው በሕግ፣ ደንብና አሰራር ላይ የሚገጥሙ ችግሮች ዙሪያ ውይይት የሚያካሂድ ይሆናል። ኮንፌደሬሽኑ ነፃና ገልተኛ በመሆን የአሰሪውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አብራርተዋል።