ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስዊድን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በስዊድን በተካሄደው የዘንድሮው ስድስተኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር አሸንፈዋል። የባውስ ጋላን ስታዲየም በዳይመንድ ሊጉ ውድድር በ31 የተለያዩ ርቀቶች የተካሄዱ የአትሌቲክስ  ውድድሮችን አስተናግዷል። በ800 ሜትር ሴቶች ጫልቱ ሹሜ 2 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ከ16 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ መሆን ችላለች። አትሌቷ በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል። ኡጋንዳዊቷ ሀሊማ ናካይ 2 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ከ37 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ የብሪታኒያ ተወዳዳሪዋ ሼልያና ኦስካን-ክላርክ 2 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ ከ9 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ 3 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ64 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን የገባችበት ሰአት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷ ሆኖ ተመዝግቦላታል። አትሌቷ በማሸነፏ ምክንያት የዳይመንድ ሊግ ነጥቧን ወደ 11 ነጥብ ከፍ ያደረገች ሲሆን በርቀቱ አትሌት በሱ ሳዶ 7 እንዲሁም አትሌት ሀብታም አለሙ 6 የዳይመንድ ሊግ ነጥብ አላቸው። የብሪታኒያ ተወዳዳሪ የሆነችው ላውራ ሙዊር 3 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ53 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ ሞሮኮዋዊቷ ራባቤ አራፋይ 4 ደቂቃ ከዜሮ ዜሮ ሴኮንድ ከ28 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ሶስተኛ ወጥታለች። በውድድሩ ላይ የተሳተፉት አትሌት በሱ ሳዶና አትሌት ሀብታም አለሙ በቅደም ተከተል 7ኛ እና 12ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋ 13 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ ከ5 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን የገባበት ሰአት በ2018 በርቀቱ ከተመዘገቡ ሰአቶች ፈጣኑ ሆኖ ተመዝግቧል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነው ብርሃኑ ባለው 13 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ ከ25 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ አትሌት አባዲ ሀዲስ 13 ደቂቃ ከ6 ሴኮንድ ከ76 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን በርቀቱ የግሉን የዓመቱ ፈጣን ሰአት አስመዝግቧል። አትሌት ዳዊት ወልዴ በውድድሩ 8ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አትሌት ሰለሞን በማሸነፉ ምክንያት 8 የዳይመንድ ሊግ ነጥብ በማግኘት አንደኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አትሌት አባዲ ሀዲስ 6 ነጥብ በመያዝ ሶስተኛ አትሌት ዳዊት ወልዴ አንድ ነጥብ በማግኘት 8ኛ ደረጃን ይዘዋል። በ800 ሜትር ወንዶች ኬንያዊው ፈርጉሰን ቼሪዮት ሮቲች፣ባህሬናዊው ሳዲቅ ሚኩና የታላቋ ብሪታኒያ ተወዳዳሪ የሆነው ጃክ ዋይትማን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቶሌሳ ቦደና 10ኛ ወጥቷል። ሰባተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በቤልጂየም ብራሰልስ ፍጻሜውን ያገኛል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም