የጥረት ኮርፖሬት ኩባኒያዎች በአክሲዮንና በሽያጭ ወደ ግል ሊተላለፉ ነው

ሀምሌ 8/2011 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በጥረት ኮርፖሬት ስር የሚተዳደሩትን ከአስር በላይ ኩባኒያዎች በአክሲዮንና በሽያጭ ወደ ግል እንዲዘዋወሩ መወሰኑን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አስታወቁ ። የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈጻሚ  አቶ አባተ ስጦታው ትናንት በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አዘጋጅነት በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የንግድ ቀን በዓል ወቅት  እንደተናገሩት ኩባኒያዎቹ በአክሲዮንና ሙሉ በሙሉ ሽያጭ ወደ ግል ለማስተላለፍ ተወስኗል ። የክልሉ ህዝብ በአሰራር ግልፀኝነት መጓደል ምክንያት በጥረት ኮርፖሬት ኩባኒያዎች ላይ  ጥርጣሬ እንደነበረው ገልጸዋ ልህዝቡ የተሟላ ጠቀሜታ ይሰጡ ዘንድ በአክሲዮንና በሽያጭ  ወደ ግል እንዲተላለፉ መወሰኑን አስታውቀዋል። በጥረት ኮርፖሬሽን  ስር ከሚተዳደሩት ኩባኒያዎች መካከል አምባሰል ንግድ ስራዎች፣ጥቁር አባይ ትራንስፖርት፣የባህር ዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ኩፓንያዎች እና  ሌሎችም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ይገኙበታል ። ከ 20 ዓመታት በፊት በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋሙት  የጥረት ኮርፖሬት ኩባኒያዎች በንግድና ትራንስፖርት ፣በማኒፋክቸሪንግና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ተግባር የተሰማሩ ናቸው ። በአሁኑ ወቅት ለ12 ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠሩት እነዚህ ተቋማት በአክሲዮንም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የክልሉ ባለ ሀብቶች በንቃት በመሳተፍ እራሳቸውም ሆነ ህዝባቸው እንዲጠቅሙ ምክትል ስራ አስፈፃሚው  ጋብዘዋል ። የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል በበኩላቸውየጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች በክልሉ ህዝብ ላይ አመኔታ አጥተው መቆየታቸውን ገልፀው "አሁን ግን  ግልፅነትን ተከትሎ ለህዝብ ጥቅም እንዲሰጡ እየተሰራ ነው "ብለዋል ። ኩባኒያዎቹ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የዋጋ መናር ለማረጋጋት ከውጪም ጭምር መሰረታዊ ዕቃዎችን በማስገባት ለህዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል ። በጥረት ኮርፖሬት ስር የሚተዳደሩት ኩባኒያዎች የአማራ ህዝብ የደርግ ስርዓት ለመገርሰስ ሲታገሉ ለነበሩ ልጆቹ ካበረከተው የገንዘብ ድጋፍ በተረፈ ገንዘብ የተቋቋሙ ናቸው ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም