ቀጥታ፡

ኮሌጁ ያሰለጠናቸው አንድ ሺህ 827 ተማሪዎችን አስመረቀ

ሀምሌ 8/2011 (ኢዜአ) የጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸው አንድ ሺህ 827 ተማሪዎችን አስመረቀ። ኮሌጁ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በዲፕሎማ መርሃ ግብር ነው፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት የኮሌጁ ዲን ዶክተር ጋልዋክ ሮን እንደገለጹት ተቋሙ ትናንት ያስመረቃቸው ተማሪዎች በትምህርትና በጤና ሙያ ዘርፍ በቀንና በማታ መርሃ ግብር ለሦስት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ በትምህርት መስክ የተመረቁ ዕጩ መምህራን ከሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች መካከል ቋንቋ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሂሳብና ማህበራዊ ሳይንስ ይገኙበታል፡፡ በጤናው ዘርፍ የተመረቁት ደግሞ ክሊኒካል ነርስ፣ ላብራቶሪና የጤና መረጃ አያያዝ  ከሰለጠኑበት ውስጥ ተጠቅሰዋል። ከተመራቂ መካከል አንድ ሺህ 480ቹ በመምህርነት ሙያ ቀሪዎቹ ደግሞ በጤና  ሙያ ዘርፍ ሲሆን ከመካከላቸውም 572 ሴቶች ናቸው። እንደ ዲኑ ገለፃ  ኮሌጁ ላለፉት 25 ዓመታት በየዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ችግርን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በትምህርትና ጤናው መስኮች የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት በመስጠት ለዘርፍ ስኬት መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመስኮቹ አገልገሎቶችን ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ለተነደፈው ግብ መሳካት በኮሌጁ የተጀመረው የሰው ኃይል ልማት ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል። የዕለቱ ተመራቂዎች በቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትወደ ተግባር በመለወጥ ህዝቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ በተለይም በክርምቱ እንደ ሀገር በተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ላይ በንቃት እንዲሳተፉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከተመራቂዎች መካከል ሊኒ ካድሪ በሰጠው አስተያየት በተማረበት የሙያ መስክ እራሱንና ህብረተሰቡን ለመጥቀም እንደሚሰራ ተናግሯል። በሰለጠነችበት ሙያ ከራሷ አልፎ ህዝቡና ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗ የተናገረችው ደግሞ ሌላዋ ተመራቂ አባበየሁ ገረመው ናት። በኮሌጁ ቆይታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ  ተመራቂዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም