የመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ የሀጅ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀኑ

77
ሐምሌ 8/2011 (ኢዜአ) የመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ የሀጅ ተጓዦች ለሀጅ ስነ-ስርዓት ዛሬ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አምርተዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ፣ በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ቢን ጃሚል አብዱላህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ላቀኑት 312 የሀጅ ተጓዦች(ሁጃጆች) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አየር መንገዱ የሀጅ ተጓዦችን ለማስተናገድ የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርጓል። እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2011 ዓም ድረስ ደርሶ መልስ አጠቃላይ 38 በረራዎችን ያዘጋጀ መሆኑንና በአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ አምስት ሺህ ተጓዦች የበረራ አገልግሎት እንደሚሰጥና ሌሎች አምስት ሺህ ተጓዦች በሳዑዲ አየር መንገድ አገልግሎት እንደሚያገኙም ተናግረዋል። የሀጅ ጉዞን በተመለከተ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አመልክተዋል። የሀጅ ተጓዦች ከነሐሴ 14 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም የሃጅ ስነ ስርዓታቸውን ፈፅመው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ይሆናል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የቦርድ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ ለሀጅ ጉዞ 15 ሺህ የሙስሊም ምዕመን መመዝገቡን ከዚህ ውስጥም የሳዑዲ አረቢያ የሀጅ ሚኒስቴር 10 ሺህ ተጓዦች ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ለቀሪዎቹ አምስት ሺህ ሰዎች ፈቃድ እንዲሰጥ ለሚኒስቴሩ ጥያቄ መቅረቡንና የሚኒስቴሩ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል። የመጀመሪያው የሀጅ ተጓዦች በረራ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም የኤሌክትሮኒክስ የቪዛ አገልግሎቱ ላይ ችግር በመግጠሙ፣ ቪዛ ቶሎ መድረስ ባለመቻሉና የውጭ ምንዛሬ በፍጥነት ባአለማግኘት መዘግየቱን ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም