ቀጥታ፡

በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ስልጠና እየተካሄደ ነው

ሀምሌ 8/2011( ኢዜአ) በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የምስራቅ አፍሪካን ፀጥታ ለማጠናከር ያለመና በኢትዮጵያ የሚካሄደው ወታደራዊ ስልጠና ዛሬ ተጀመረ ወታደራዊ ስልጠናው በዋናነት በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዩ ኃይል (አሚሶም) የሰላም ማስከበር ስራን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 በላይ አገሮች የተውጣጡ ወታደሮች ይሳተፉበታል። ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፉ በአሜሪካ መንግስት የሚሸፈንና እርስ በርስ መማማርን መሰረት ያደረገ መሆኑን በዛሬው እለት በስልጠናው መክፈቻ ላይ በተሰጠው መግለጫ ተነስቷል። ስልጠናው በወትድርና ውስጥ የሚካሄዱ የማጥቃትና የመከላከል፣ የህክምና አሰጣጥ፣የጋዜጠኞች የዜና አዘጋገብ፣ ወታደራዊ ቁሳቁሶች (ሎጂስቲክስ) አቀራረብና ሌሎች ዘርፎችንም ያካትታል። በአፍሪካና በደቡብ አውሮፓ የአሜሪካ የጦር አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሮጀር ክላውቴር በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ በቀጠናው የሚታዩ የአሸባሪነት እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁሉም አገሮች ስጋት ነው ። በተለይም በቀጠናው እየተበራከቱ የመጡት የሽብርተኝነት ድርጊቶች፣ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ድርጊቶች የቀጠናውን አገሮች ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ አጋሮች በቅንጅት በመስራት ልንከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል። ''ኢትዮጵያ በአሚሶምና በሌሎች አለም አቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ተሳትፎ አድንቀው አሁን የሚካሄደው ስልጠና ይህንኑ የሚያሳድግ ነው'' ብለዋል። የኢፌዴሪ መንግስት የሰላም ማስከበር ዋና ሃላፊ ተወካይ ብርጋዴር ጀኔራል ሃብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው ስልጠናው በቀጠናው ያሉ አገሮች የተሳተፉበት መሆኑ የቀጠናውን ሰላም በጋራ ለማስከበር የሚያስችል እንደሚሆን አመልክተዋል። አሚሶም በቀጠናው ያለውን የሰላም ማስከበር ስራ ከማጠናከር ባሻገር አገሮቹ በራሳቸው ያላቸውን ወታደራዊ አቅም እንዲያጠናክሩ የሚያስችልና ሽብርተኝነትን በራሳቸው ለመከላከል የሚያስችል ዓቅም ይፈጥርላቸዋል። በስልጠናው ከሚሳተፉ አባላት መካከል ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ርዋንዳ፣ ጀርመን የሚገኙበት ሲሆን አፍሪካ፣አውሮፓና አሜሪካን የቀጠናውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት አስተሳስሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ስለመሆኑ ተነግሯል። በስልጠናው በሚሳተፉ ወታደሮች ብዛት ኢትዮጵያና አሜሪካ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ባጠቃላይ  ከ1 ሽህ 100 በላይ ወታደሮች ይሳተፋሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም