የከተማ አስተዳደሩ በቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ አስተዳደሩ በቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 7/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 8 ሺ 492 ተማሪዎችን አስመርቋል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ተመራቂዎቹ በስልጠናው ያገኙትን ክህሎትና እውቀት ለአገሪቷ ልማትና እድገት እንዲያውሉት መልዕክት አስተላልፈዋል። ኤጀንሲው ያሰለጠናቸው ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 በተለያዩ የሙያ አይነቶች መሆኑን ገልጸው የሚኖራቸው አገራዊ አስተዋጾም ላቅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ አሁን ካለው ፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ መልካም እድል እንዳላቸው ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩም በዚሁ ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግ የሁለት ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልጸዋል። ወጣቶቹ ስራ በመፍጠር ላይ ትኩረት አድርገው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ጠቁመው ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም እንደገለጹት በአለም ላይ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በርካታ አገሮች በቴክኒክና ሙያ እድገታቸውን ማሳካት ችለዋል።
ይህንንም መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ወጣቶች ክህሎትና እውቀትን ያጣመሩ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ለታሰበው እድገትና ልማት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል። "በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን የምንፈልገው እድገት ላይ ለመድረስ ጊዜ አይፈጅብንም" ሲሉም ተናግረዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት እንደ ሃገር ለቴክኒክና ሙያ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። የስራ ፈጠራን ለማበረታታት የከተማ አስተዳደሩ 2 ቢሊዮን ብር መመደቡም ጥሩ እድል ነው ብለዋል። ይህም ለተመራቂዎች መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው ለስራ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ተመራቂዎቹ ከኮሌጆቹ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር 50 ሺህ ደብተር፣ 50 እሽግ እስኪርብቶና እርሳስም በበጎ ፈቃደኝነት ያበረከቱ ሲሆን በእለቱም የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።