ተመራቂዎች ዘረኝነትና ጎሰኝነትን በመታገል ሀገርንና ህዘባቸውን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች ዘረኝነትና ጎሰኝነትን በመታገል ሀገርንና ህዘባቸውን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተመለከተ
አምቦ /ደብረብርሀን /ኢዜአ/ሐምሌ 6 /2011 ተመራቂ ተማሪዎች በሚሰማሩባቸው የስራ መስኮችና አካባቢዎች ሁሉ ዘረኝነት፣የጎጠኝነትና የአካባቢያዊት አስተሳሰቦችን አጥብቀው በመታገል ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተመለከተ ። የአምቦና ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 8ሺህ 749 ተማሪዎችን ዛሬ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አስመርቀዋል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ስነ ስርአት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባል ወይዘሮ ሕይወት ሞሲሳ ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀት ስራን ሳይንቁና ሳይጠብቁ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል። የዘረኝነት፣የጎጠኝነትና የአካባቢያዊት አስተሳሰቦችን በመታገል ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ተመለከተ። “ሀገሪቱን በልማትና ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተማረና ሰለጠነ የሰው ኃይል ጠቀሜታው የጎላ ነው”ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አጣምረው ለሃገራቸው የሚጠቅም ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ማህበረሰቡን ያሳተፉ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ። "የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ነው” ያሉት ዶክተር ታደሰ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመንግስትና ከለጋሽ ድርጅቶች በተመደበ 25 ሚሊዮን ብር የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በህክምና ትምህርት አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ በጀመረው ፕሮጀክት ከ500 ለሚበልጡ የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች የነጻ ህክምና አገልግሎ መስጠቱን ጠቅሰዋል ። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አራት ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ መሃመድ እድርስ በተሰማራበት መስክ ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ቀጣይነት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጻል ። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው 5ሺህ 685 ተማሪዎች መካከል 2ሺህ202 ሴቶች ሲሆኑ የዩኒቨርስቲው አጠቃላይ የቅበላ አቅሙም 30 ሺህ መድረሱ ታውቋል ። በተመሳሳይ የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ በ49 የትምህር አይነቶች ያሰለጠናቸውን 3ሺህ 64 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል ። ከአካውንቲግ ትምህርት ክፍል 3ነጥብ 96 በማምጣት የመዳሊያና የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ኤፍራታ ብርሃኑ በሰጠችው አስተያየት በቀሰመችው እውቀት ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግራለች። በተጨማሪ ለወጣቶች ስለ ሰላም በመስበክ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የድርሻዋን እንደምትወጣ ገልጻለች ። በህግ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና የመዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ትእግስት ደሳለኝ በበኩሏ “በተማርኩበት የሙያ ዘርፍ ፍትህ ለሁሉም እኩል በመስጠት ማህበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ” ብላለች ። የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ደረጀ አንዳርጌ ተመራቂ ተማሪዎች ሳይማር ያስተማራችሁን ህዝብ በታማኝነትና በቅንንነት እንዲያገለግሉ መልእክት አስተላልፈዋል ። “ኢትዮጵያዊትነትን በውስጣችሁ ይዛችሁ በምትሰማሩበት የሙያ መስክና አካባቢ ከሚኖር ማህበረሰብ ጋር በመከባበር፣ በመቻቻልና ጥላቻን በማስወገድ ለእድገት ልትሰሩ ይገባል” ሲሉ መክረዋል። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 41 በመቶው ሴቶች ናቸው ።