ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጣቸው - ኢዜአ አማርኛ
ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጣቸው
ሐምሌ 6/2011 (ኢዜአ) አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ከ9 ሺህ በላይ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ስነ ስርዓት ላይ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን ለሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ያበረከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ናቸው። ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እና አቶ ተወልደ ለክብር ዶክትሬት ዲግሪው የበቁት ከሚመሯቸው ተቋማት ባለፈ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንደዚሁም ምጣኔ ኃብታዊ እድገትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላላት ተቀባይነት ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በስነ-ስርዓቱ ላይ ገልፀዋል። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ኩባንያውን እየመሩ ያሉት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አየር መንገዱን በሶስት እጥፍ በማሳደግ፣ በዚህ ስኬትም የበርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤት ያደረጉና አገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ እንድትሆን ያስቻሉ መሆናቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል። አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በተለይ አገሪቷ የአፍሪካ ዋነኛ መዳረሻ፣ ብሎም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር የአፍሪካ ህብረትን ራእይ ለማሳካት የሚያስችል ውጤታማ አመራር መስጠታቸውም ተነግሯል። አቶ ተወልደ በሚመሩት አየር መንገድ እያሳዩት ባለው ስኬት አማካኝነትም ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የቦርድ አባልና ኃላፊ በመሆንም እያገለገሉ እንደሚገኙም ተጠቁሟል። ከእነዚህም መካከል የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር፣ የፓን አፍሪካ አቪየሽን ኢኒሺዬቲቭ፣ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀኃፊ የዘላቂ ትራንስፖርት ልማት ከፍተኛ መማክርት ተጠቅሰዋል። ይህ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቡት ስኬት እውን የሆነው አቶ ተወልደ ባሳዩት ፅናትና ትጋት መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ ይህም ለሌሎች ወጣት ኢትዮጵያዊያን ትምህርት ይሆን ዘንድ ለአቶ ተወልደ እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል። ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመርም ከህጻንነት እድሜያቸው ጀምሮ ሃይማኖታዊ እውቀትን ለመቅሰም ያሳለፉት ውጣ ውረድ፣ ይህንን እውቀታቸውንም ለሌሎች ለማስተላለፍ እያሳዩ ያለው ፅናትና ትጋት በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ኣርኣያ ሊሆን የሚችል ታላቅ ተግባር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል። ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር በተለይ ሃይማኖታዊ እውቀታቸውን ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ከ50 በላይ መፅሃፎችን ፅፈዋል፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የሚጠቀሙበትን ቅዱስ ቁርኣን ከአረብኛ ወደአማርኛም ተርጉመዋል። በእምነት የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር በአብዛኛው የህይወት ዘመናቸው ያሳዩት ትጋት ለአገር ተረካቢ ወጣቶች ታላቅ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል መሆኑንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው አመልክተዋል። ሐጂ ኡመር የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መሪ ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባል፣ የኢትዮጵያ ኡለማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ በመሆንም የእምነቱ ተከታዮችን በታማኝነትና በብቃት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚስተዋሉትን አለመግባባቶች ተከትሎ የሚፈጠሩ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል እንዲገቱም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መልዕክቶችን በማስተላለፍ የአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ያሉ የሃይማኖት መሪ መሆናቸውም ተወስቷል። በኢትዮጵያ የእስልምና ተከታዮች፣ እንደዚሁም በእምነቱ መሪዎችና መንግስት መካከል ተፈጥረው የነበሩ ልዩነቶች እንዲወገዱና መግባባት እንዲሰፍንም ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውም ተነስቷል። ይህ ተግባራቸው በልዩነቱ ሳቢያ በአገሪቱ ሊከሰት ይችል የነበረውን አደጋ በመግታት ምእመኑ እንዲረጋጋ፣ የአገሪቷ ሰላምና መረጋጋትም እንዳይደፈርስ የበኩላቸውን ኃላፊነት የተወጡ ታላቅ ዜጋ መሆናቸውም ተገልጿል። በዚህ ተግባራቸውም በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ክብርንና ዝናን ማትረፋቸውንም ፕሮፌሰር ጣሰው ገልፀዋል። ሁለቱ ተላላቅ ተሸላሚ ሰዎችም ይህ የክብር ዶክተሬት የግላቸው ውጤት ብቻ ሳይሆን የስራ ባልደረቦቻቸውም ጭምር መሆኑን አውስተው፤ የነገ አገር ተረካቢ ተመራቂዎችም የእነሱ ተሞክሮ ቀስመውና አገርን በላቀ ሁኔታ በማገልገል የዚህን ዓይነት ድርብ ክብር ለመጎናጸፍ እንድሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።