ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ጤና ተቋማት ቅጥር ግቢና አካባቢ ከ100 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል

አዳማ/ኢዜአ/ ሐምሌ 06/2011 በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት ቅጥር ግቢና አካባቢ ከ100 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለፁ። የኢትዮጵያ የምግብ መድኋኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት በአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ  ችግኝ ተክለዋል። የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህን ወቅት እንደገለፁት የጤና ተቋማትን ፅዱ፣ ውብና አሩንጓዴ ማድረግ ለተገልጋዩ ህብረተሰብም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ጤና አስፈላጊ ነው። የጤና ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ውጤታማ ለመሆን አካባቢያቸውን ማፅዳትና ማስዋብ መቻል እንደሚገባቸውም ኃላፊው አስገዝበዋል። "ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በአረንጓዴ ልማት ላይ የያዙትን ራዕይ ለማሳካትና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የጤና ባለሙያዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ስትራቴጂ ቀይሰን እየሰራን ነው "ብለዋል። በክልሉ በሚገኙ ከ7 ሺህ በላይ የጤና ኬላዎች ፣ በ1ሺህ 600 የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ ሠራተኞችና በክልሉ የጤና ዘርፍ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች በመተባበር ከ100 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል። የተተከሉትም በጤና ተቋማቱ ቅጥር ግቢና አካባቢዎች እንደሆነ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት በአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ ተገኝተው የተከሉት ችግኝም የእቅዱ አካል እንደሆነም ዶክተር ደረጄ ጠቁመዋል ። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው ጤናና አረንጓዴ ልማት የማይለያዩ በመሆናቸው የጤና ተቋማትን በማስዋብ ህብረተሰቡንና ራሳችን ከተበከለ አየር ለመጠበቅ ችግኝ በመትከል ድጋፋቸው ገልጸዋል። የባለስልጣኑ ሠራተኞች በ17ቱ የመግቢያና የመውጫ ኬላዎችና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም ተመሳሳይ  የችግኝ ተከላ እንደሚያደርጉ  ጠቅሰዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም