በሀረሪ 45 ሺህ ወጣቶች በክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ 45 ሺህ ወጣቶች በክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል

ሐረር /ኢዜአ/ ሐምሌ 6 / 2011 በተያዘው የክረምት ወቅት በተሰማሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ ተግባር ለማከናወን መዘጋጀታቸውን በሐረሪ ክልል ወጣቶች ገለጹ። በሀረሪ 45 ሺህ ወጣቶች በክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አስታውቋል። ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል በሀረር ከተማ የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ ወጣት ክሩቤል ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ስራ ማከናወኑን አስታውሷል። ያለፈውን ተሞክሮው ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት መነሳሳት እንደፈጠረለት የገለፀው ወጣቱ በተለይ አቅመ ደካማ አረጋውያንና ማህበረሰቡን መርዳት እርካታ እንደሚሰጠው ተናግሯል ። ዘንድሮም የተሻለ ተግባራት ለማከናወን በበጉ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፉን አስረድቷል ። የአቦከር ወረዳ ወጣት ዳንኤል አበበ በበኩሉ በየክረምቱ የሚሳተፍበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስራ ፍቅር እንዲያድርበት እንዳደረገው ገልጿል። ዘንድሮም ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠትና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማከናወን በወጣት አደረጃጀቱ በኩል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁሟል ። " የመረዳዳት ባህላችን እንዲጎለብትና ተነሳሽነታችን እንዲጨምር የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልናል "ያለው ደግሞ የአባድር ወረዳ ነዋሪው ወጣት ፋሲካ ፍቃዱ ነው። ባለፈው ዓመት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸውን የተጠገነላቸው በሸንኮር ወረዳ 09 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብዙነሽ ዘውዴ በሰጡት አስተያየት ወጣቶች ባደረጉላቸው ድጋፍ ከችግር መላቀቃቸውን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል ። የሀረሪ ክልል ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም እንደገለጹት 45 ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የዘንድሮ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከትላንት ጀምሮ በክልሉ ሁሉም የከተማና የገጠር ቀበሌዎች ተሰማርተዋል። ለሁለት ወራት በሚቆየው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ የሚሳተፉት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤቶች ፣ ከወጣቶች ማህበራትና ከወጣቶች ሊግ የተውጣጡ ወጣቶች ናቸው ። ወጣቶቹ ቆይታቸው በተመረጡ 8 ቦታዎች ላይ ከ35 ሺህ በላይ የዛፍ ችግኝ ተከላ ያከናውናሉ ። "የ70 አረጋውያን ቤት የማደስና የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ይካሄዳሉ "ያሉት ኃላፊዋ ወጣቶቹ 2 ሚሊዮን 500ሺህ ብር ብር የሚገመት የልማት ስራዎች የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ዘንድሮ ወጣቱ በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ በሰላምና በመቻቻል የአብሮነት ባህልን በማሳደግ ለስራው ትኩረት መስጠቱን ወይዘሮ አሚና አመልክተዋል።