ኦነግ ሸኔ በሚል የሚንቀሳቀሰው ኃይል አሮሞን አይወክልም- የቂልጡ ካራ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኦነግ ሸኔ በሚል የሚንቀሳቀሰው ኃይል አሮሞን አይወክልም- የቂልጡ ካራ ወረዳ ነዋሪዎች
ነቀምት ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 በኦነግ ስም የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት የሚያውከው ኃይል የኦሮሞን ህዝብ እንዳማይወክል በምዕራብ ወለጋ የቂልጡ ካራ ወረዳ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን ገለፁ። ነዋሪዎቹ ትላንት ባካሄዱት ሰልፍ “ እራሱን ኦነግ ሸኔ በሚል በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ኃይል ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የቆመ ባለመሆኑ እናወግዘዋለን” ብለዋል። ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ ስንታየሁ ባይሳ በሰጡት አስተያየት ኦነግ ሸኔ በሚል በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የተሰማራ መሆኑን ተናግረዋል። "ይሄ ኃይል የህብረተሰቡን ኑሮ በማናጋት የሚታወቁና የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል ነው” ሲሉ ነዋሪዎቹ ባሰሙት መፈክር ገልጸዋል። ወይዘሮ ሮማን መላኩ በበኩላቸው እራሱን ኦነግ ሸኔ ብለው የሚጠራው ኃይል የግል ጥቅሙንና ፍላጎቱን ለማሟላት በጫካ ውስጥ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተናግረዋል ። “ኦሮሞንና ሌላውን ብሄር በማጋጨት ለማለያየት የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው እናወግዛቸዋለን “ ብለዋል ። “ለዘመናት አንድነቱና ፍቅሩ ተጠብቆ የቆየውን የኢትዮጰያ ህዝብ በማለያየት የራሱን ፋይዳ ለማሟላት የሚንቀሳቀሰው ሸኔን እንቃወማለን “ ያሉት ደግሞ አቶ እንዳለ ፉፋ ናቸው። “የጥፋት እንጂ የልማት ራዕይ የሌላቸውን ፀረ ሰላም ሀይሎች ለማጋለጥ ዝግጁ ነኝ” ሲሉ ተናግረዋል ። በአማራ ክልልና በመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ላይ የተፈፀመው ግድያዎችን ሰልፈኞቹ አውግዘዋል። የቂልጡ ካራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ኦሊቃ የወረዳው ህዝብ ሰላሙንና ጸጥታውን የሚያውከው እራሱን ኦነግ ሸኔ ብለው የሚጠሩ ሀይል ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዱ የሚደገፍ መሆኑን ተግረዋል ። በሰልፉ ብዛት ያላቸው የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ታውቋል ።