ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰራተኞችና አመራሮች በለገጣፎ ከተማ የችግኝ ተከላ አካሄዱ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብሩን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰራተኞችና አመራሮች በለገጣፎ ከተማ የችግኝ ተከላ አካሄዱ። በለገዳዲ ለገጣፎ በተካሄደው የፌዴሬሽኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል። የፌዴሬሽኑ ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ ችግኝ መተክል ብቻ ሳይሆን በመንካከቡም በኩል ፌዴሬሽኑ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ተናግረዋል። የተተከለው ችግኝ ዘላቂ እንክብካቤ የሚደረገው ከለገጣፎ ከተማ አስተዳደርና ለገዳዲ ለገጣፎ አትሌቲክስ ክለብ ጋር በመሆን እንደሆነም ጠቁመዋል። በተለይም ቦታው አትሌቶች ልምምድ የሚሰሩበት አካባቢ በመሆኑ በየጊዜው ያለበትን ሁኔታ ለማየትና ለመንከባከብም አመቺ እንደሆነ ተናግረዋል። አትሌት ደራርቱ አገር አቀፉን የችግኝ ተከላ ሁሉም በያለበት ሊተገብረው እንደሚገባ በመግለጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አትሌቶችም ይህን መሰል የችግኝ ተከላ ስራ መከናወኑ አትሌቶች በንጹህ አየር ልምምዳቸውን ለማድረግ ያግዛቸዋል ብለዋል። በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እንዲሳተፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በደስታ መሆኑን ተናግረዋል። በአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር መሰረት በክረምቱ መላው ህዝብ የሚሳተፍበት የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ የማካሄድ ተገግባር የተጀመረ ሲሆን የግብርናና ደንን ጥምረትን የያዙ ለምግብነትና ለካርበን ስበት የሚያገለግሉ የዛፍ ችግኞች ይተከላሉ። አንድ አራተኛ የሚሆኑት ወይም አንድ ቢሊዮን ችግኞች የእንጨትነት ባህሪ ያላቸው አገር በቀል ችግኞች ናቸው። የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ ለአንድ ተቋም የሚተው ሳይሆን በርካታ ተቋማት በባለቤትነት በጋራ የሚተገብሩት እንደሚሆን ይጠበቃል። እያንዳንዱ ዜጋ በነብስ ወከፍ 40 ችግኞች እንዲተክል ታሳቢ ያደረገ የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ዘመቻ ንቅናቄ መጀመሩ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም