በድሬዳዋ 60ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ 60ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ
ድሬዳዋ ሐምሌ ኢዜአ 5/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር ከ60ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ። “በጎ ፈቃደኝነት ለአገራዊ ለውጥ!" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው አገልግሎት ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያድን ተመልከቷል ። የአስተዳደሩ ስፖርትና ወጣቶች ኮሚሽነር አና ዑመር አገልግሎቱ ትናንት በይፋ በተጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት ወጣቶቹ እስከ መስከረም 2012 በሚዘልቀው አገልግሎት ይሳተፋሉ። በበጎ ተግባር ሥራ በመሳተፍ ሌላውን መርዳት የህሊና ዕረፍትና ደስታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል ያሉት ኃላፊዋ፣ወጣቶቹ በኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከል፣ በትራፊክ ማስተናበር፣ በአካባቢ ጥበቃና ክብካቤ፣ በፅዳትና ውበት ፣በአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታና ጥገና ይሳተፋሉ ብለዋል ። “በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ይከናወናሉ” ብለዋል ። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች ለተማሪዎች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጡም ኃላፊዋ ተናግረዋል ። የድሬዳዋ ወጣቶች ኮንፌደሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ወጣት ኤፍሬም “በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ አንድ ሚሊዮን ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራ በማከናወን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ጥሪ ተግባራዊ ይደረጋል” ብሏል ። በተጨማሪም የ560 አቅም የሌላቸው ሰዎች ቤቶች ጥገናና የደም ልገሳ እንደሚደረግም ገልጿል ። ከበጎ ፍቃደኞች መካከል ወጣት አብዲ ኢብራሂም በሰጠው አስተያየት “ከምንኖርበት ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ በመሄድ በልማት ሥራ በመሳተፍ እርስ በእርሳችንና ከማህበረሰቡ ጋር ያለንን ፍቅርና አንድነት እናጠናክራለን” ብሏል። የኢትዮጵያ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ በክረምት ወራት የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን፣አገልግሎቱን በበጋ ወራት ጭምር ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።