አገሪቷ እያመነጨች ካለው ገቢ አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ በቂ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
አገሪቷ እያመነጨች ካለው ገቢ አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ በቂ አይደለም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 5/2011 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያመነጨ ካለው ገቢ አኳያ በ2011 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ በቂ አለመሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያመነጨ ካለው ገቢ አኳያ በ2011 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ በቂ አለመሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር አዳነች አቤቤ ገለጹ። ሚኒስትሯ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዳብራሩት ካለፉት ዓመታት ከተሰበሰበው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ግን በበጀት ዓመቱ የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ 213 ቢሊዮን ብር እንዲሰበስብ አቅጣጫ ያስቀመጠ ቢሆንም ተቋሙ የገቢ ዕቅዱን ከፍ በማድረግ 241 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ነበር አቅዶ ሲሰራ የቆየው። ከዚህ ውስጥም 198 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 80 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት። ይህ አፈጻጸም ከገቢ መለኪያዎች አኳያ ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንደሆነም ያነሳሉ። በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ከ2010 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። የገቢ አሰባሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን በተለይም በተያዘው በጀት ዓመት ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይሁንና የተሰበሰበው አገሪቷ ከምታመነጨው ገቢ አኳያ በቂ አለመሆኑን ይገልጻሉ። ሚኒስቴሩ በገቢ አሰባሰብ ላይ ያሉበትን ማነቆዎች ለመፍታት ያደረጋቸው ጥረቶች ማለትም የአሰራር ማሻሻያዎች፣ ለታክስ አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ለገጠማቸው ግብር ከፋዮች የተራዘመ የአከፋፈል ስርዓት መዘርጋት በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ የተሻለ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ናቸው። በበጀት ዓመቱ የተደረገው የታክስ ንቅናቄም በታክስ ከፋዩና በግብር ሰብሳቢው መካከል የነበረውን መራራቅ በማጥበብ አብሮ የመስራት መንፈስን ያመጣ መሆኑንም አንስተዋል። በአገሪቷ አሁንም ድረስ ያልተፈታውን የግብር ስወራ ለማስቀረት ከማስተማር ስራው ጎን ለጎን ህግን የማስከበር ተግባር መከናወኑንም ወይዘሮ አዳነች ገልጸዋል። በሌላ በኩል 231 ድርጅቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ኦፕሬሽን ተደርጎባቸው ችግር የተገኘባቸው በመሆኑ 306 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉንና ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዳደራዊ ቅጣት መቀጣታቸውንም አንስተዋል። እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ተቋማቸው በ2012 በጀት ዓመት 248 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል። ከዚህ ውስጥ ከአገር ውስጥ ታክስ 150 ነጥብ 1 ቢሊዮን፣ ከጉምሩክ ደግሞ 98 ነጥብ 2 ቢሊዮን ነው ለመሰብሰብ የታቀደው። ዕቅዱን ለማሳካትም አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ወይሮ አዳነች ይገልጻሉ። በአገሪቷ የሰላምና መረጋጋት እጦት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ኮንትሮባንድ እንዲሁም ኢ-መደበኛ ንግድ ደግሞ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ገቢውን በአግባቡ እንዳይሰበስብ ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል እንደሆኑ ተጠቅሰዋል።