የዋጋ ጭማሪ ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው በደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ጭማሪ ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው በደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
ሀምሌ ደሴ ኢዜአ 5/2011 በምርቶች ላይ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። የከተማው አስተዳደር የኑሮ ውድነት የሚረጋጋበትን መንገድ ለመሻት ከነዋሪዎች ፣ ከነጋዴዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል ። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰዓዳ ታደሰ እንዳሉት በመሰራዊ ምርቶች ፣ ሸቀጦች ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያለ አግባብ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ጫና ፈጥሮባቸዋል። “መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማስተካካያ ካላደረገ የቀጣይ ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል” ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ሰዓዳ ገለጻ ኪሎው ምስር ከ40 ወደ 80 ብር ፣ ነጭ ሽንኩርት ከ45 ብር ወደ 90 ብር፣ ቲማቲምና ቀይ ሽንኩርት ከ12 ብር ወደ 25 ብር ከፍ ብሏል፡፡ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አቡበከር አራጋው በበኩላቸው" ከግንቦት ወር ጀምሮ በየጊዜው በነጋዴው ስምምነት ብቻ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ቤተሰቦቻችንን በአግባቡ እንዳንመራ አድርጎናል" ብለዋል፡፡ የፋብሪካ ውጤቶች፣የግብርና ምርቶች፣የግንባታ እቃዎችና ሌሎች መሰረታዊ ምርቶች በእጥፍ መጨመራቸውን አመልክተዋል። በተለይ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ሸማቹና አምራቹ እንዳይገናኝ በማድረግ የግብይት ሥርዓቱን በማዛበት ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው ተናግረዋል። ኪሎ ስጋ ከ200 ወደ 300 ብር ፣ ሙዝ ከ20 ብር ወደ 35 ብር፣ ምግብ ቤቶችም ከ20 ብር በታች ይሸጧቸው የነበሩ የምግብ አይነቶችን ከ40 ብር በላይ ማስገባታቸውን ጠቅሰዋል። በኑሮ ውድነት አሳበው አለአግባብ የጸጥታ ችግር እንዲከሰት የሚጥሩ ግለሰቦች ላይ መንግስት በጥናት ታግዞ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ። በደሴ ከተማ በካፌና ሬስቶራንት ስራ የተሰማሩ አቶ አባይነህ አየለ በሰጡት አስተያየት "በአንድ እቃ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በሌሎች ነገሮች ላይ ጭማሪ እንዲደረግ ምክንያት ይሆናል "ብለዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ሽመልስ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የኑሮ ውድነት የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍጠሩን ገልጸዋል። " መምሪያው ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ባደረገው የገበያ ጥናት የምርት እጥረት ሳይከሰት ነጋዴው ተመካክሮ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ተረጋግጧል"ብለዋል ። ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 113 ነጋዴዎች ላይ ከጹህፍ ማስጠንቀቂያ የንግድ ድርጅታቸውን እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል። በግብርና ፣ ኢንዱስትሪ፣ እንሰሳትና እንሰሳት ተዋጽኦ እንዲሁም ምግብ ቤቶችና ሌሎችን ያልተገባ የዋጋ ንረት ተስተውሎባቸዋል። አቶ ወንድወሰን እንዳሉት ከተለያዩ ክልሎች፣ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ ምርቶች ላይ ጥናት ተደርጎ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል። “በንግድ ቤቶች ላይ የተሻሻለን የዋጋ ዝርዝር ህጋዊ ማህተም በማድረግ ስለለጠፍን ህብረተሰቡ የሚገዛውን ማንኛውንም ምርት የዋጋ ንፅፅር በማድረግ መብቱን ማስከበር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡ የዋጋ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ምርቶች መካከል ጤፍ በኩንታል ከ3ሺህ ብር በላይ የነበረው ከ2ሺህ 700 ብር በታች፣ ስጋ በኪሎ እስከ 350 የነበረው በደረጃ ከ220 እስከ 280 ብር ዝቅ ብሎ እንዲሸጥ መወሰኑን ጠቅሰዋል። የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ጫኔ በበኩላቸው የምርት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም ከክልልና ከፌደራል መንግስት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።