ቀጥታ፡

ተመድ የኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ ልማት ስራዎችን ማድነቁ ተገለጸ

ሐምሌ 4/2011 ( ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ ልማት ስራዎችን ማድነቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግስታት በድንበሮቻቸው አካባቢ እያካሄዱት ያለው ልማት ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው። የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአፍሪካ የሽብርተኝነት እና ፅንፈኝነት አደጋዎች ላይ ሐምሌ 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም ናይሮቢ ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የድንበር አካባቢ ልማቱ ግጭትን ለማስወገድ ይጠቅማል። የልማት እንቅስቃሴው የድንበር ላይ ውዝግብና ግጭቶችን ከመቀነስ ባለፈ ፅንፈኝነትን ለመከላከል እንደሚረዳም ገልጸዋል። በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ከተጀመረ አራት አመት የሆነው የድንበር ተሻጋሪ ልማት በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የሚከሰተው ግጭት እንዲቀንስ እንዳደረገ ተናግረዋል። አሸባሪነትንና ፅንፈኝነትን በጦርነት ብቻ ለመከላከል አይቻልም ያሉት አምባሳደሩ ድህነትን መቅረፍ፣ መገለልን ማስቆም ትምህርትን ማስፋፋትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ዕርምጃዎችን አገራት መውሰድ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። በናይሮቢው ስብሰባ ላይ ከ100 አገሮች በላይ የተወከሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳታፊ ሆነዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የአገሮቹን እድገትና ብልፅግና ሊያፋጥኑ በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ባለፈው ዓመት ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደሃላፊነት በመጡ ሰሞን በኬንያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በግብርና ልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በወታደራዊና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከል በትብብር ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል። ከአይሲዮሎ - ሞያሌ - አዲስ አበባ የሚዘልቅ መንገድ እንዲሁም ከናይሮቢ አዲስ አበባ የሚደርስ የባቡር ትራንስፖርት ለመዘርጋት እንዲሁም የላሙ-ጋሪሳ-አይሲዮሎን እና የሞያሌ- ሀዋሳ-አዲስ አበባ መንገድ ፕሮጀክትን በጋራ ለመቆጣጠርና ለመከታተልም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይታወቃል። የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል የገባ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስትም በበኩሉ በሚያገኘው መሬት ላይ የሎጂስቲክ እንቅስቃሴ መገልገያዎችን የሚያለማ መሆኑን አረጋግጧል። ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑባትን ሞያሌ "የጋራ ከተማና የኢኮኖሚ እንብርት" ለማደረግ የሚያስችል ስምምነት በሁለቱ አገሮች መንግስታት ከስምምነት መደረሱ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሚያጠናክር ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም