በጋምቤላ የፀጥታ ችግር በሚፈጥሩ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል--- ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የፀጥታ ችግር በሚፈጥሩ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል--- ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉ
ሐምሌ 4/2011 ( ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ወጣቱን ኃይል በመገፋፋት የጸጥታ ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስጠነቀቁ። በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት ከጎሰኝነትና ከቡድንተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሊሰሩ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ። በጋምቤላ ክልል የጸጥታና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተካሔዷል ። ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይት መደረኩ እንደገለጹት በክልሉ ቀደም ሲል የነበሩት የጸጥታ ችግሮች ተወግደው የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳግም የማገርሸት ምልክቶች መታየት ጀምረዋል ። በተለይም በጋምቤላ ከተማ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ግጭት ሊባል ባይችልም ባልታወቁ ሰዎች የዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቀዋል። የክልሉ መንግንስትና የድርጅቱ አመራር አካላት የችግሩን መንስኤ ለማጣራት ባደረገው ግምገማ በአመራሩ ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ያለመኖር ክፍተት እንዳለ መታየቱን ተናግረዋል ። አመራሩ ከቡድንተኝነት፣ ከጎሰኝት ከጠባብ ብሄረተኝነትና ከስልጣን ሽኩቻ እንዳልተላቀቀም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል ። በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ አካላት ወጣቱን ወደ ግጭት በመገፋፋት ስውር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አቶ ኡሞድ ገልፀው" መንግስት የህግ የበለይነትን ለማስከበር ፓለቲካዊና ህጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚገደድ ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቃዋል። በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ከቡድንተኝነት፣ ከጎሰኝነትና ሌሎች መጥፎ አመለካከቶች በመውጣት ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ከመድረኩ ታሳፊዎች መካከል አቶ ዩኒያስ አበበ በሰጡት አስተያየት" በክልሉ በተደጋገሚ የጸጥታ ችግር እየተከሰተ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ ባለመወሰዱ ነው" ብለዋል። "የአመራር አንድነት ሊፈጠር ያልቻለው የስልጣን ሽኩቻ የፈጠራቸው ችግሮች ናቸው" ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አኳይ አቡቲ ናቸው። አመራሩ ከስልጣን ሽኩቻ በመውጣት የአስተሳብና የአመለካከት አንድነቱን ሊያጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል ። ሌላው ተሳታፊ አቶ ፒተር ሆው በበኩላቸው በድርጅቱ ውስጥ የከፋ የአመለካከት ችግር እንደሚታይበት ገልጸው " የማስተካከያ እርምጃዎችን ሊወሰድ ይገባል " ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።