የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሌላቸውና ያላደሱ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት አይችሉም---ኤጀንሲው - ኢዜአ አማርኛ
የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሌላቸውና ያላደሱ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት አይችሉም---ኤጀንሲው
አዳማ ሀምሌ 4/2011(ኢ ዜ አ) በሀገሪቱ የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሌላቸውና ያላደሱ ማንኛውም ዓይነት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጄንሲ አስታወቀ። ኤጄንሲው የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋንን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የዘመቻ ምዘገባ ለመጀመር በሚያስችለው ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መክሯል ። በዚህ ወቅት የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ እንደገለጹት በሀገሪቱ ካሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ተመዝግበው የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን አባል የሆኑት 55 በመቶ ብቻ ናቸው። ተሽከርካሪዎችን በሙሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ለአንድ ወር የሚቆይ ምዝገባ በዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል ። "ከሐምሌ 10 እሰከ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሚቆየው ዘመቻ ከ450 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል" ያሉት ዳይሬክተሯ በጊዜ ገደቡ ቀርበው ያልተመዘገቡና ያላደሱ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መሰጠት እንደማይችሉ አስታውቀዋል። የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ፣ ተጎጂዎች ተገቢውን ህክምናና የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ለማስቻል የሚረዳ መሆኑን አብራርተዋል ። በኤጄንሲው የእቅድና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሰረት ገብረኪዳን በበኩላቸው 42 ህዝባዊ አደረጃጀቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዘመቻ ምዝገባው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ምዝገባውንና የቁጥጥር ሥራውን የተቀናጀ ለማድረግ የድርጊት መረሃ ግብር መዘጋጀቱን አመልክተዋል። "በየዓመቱ ከ66ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ተመዝጋቢ ቢሆኑም በሀገሪቱ ካለው ሀብት እንፃር አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገበ አልተቻለም " ብለዋል ። በተሰጣቸው ጊዜ መመዝገብ ያልቻሉ ተሽከርካሪዎች መንገድ እንዳይጠቀሙ ከማድረግ ባሻገር ህጋዊ የቅጣት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ከክልል እስከ ፌደራል ያሉ የትራፊክ ፖሊሶች፣ ዐቃቤ ህጎችና ፍርድ ቤቶች በቅንጅት የሚሰሩበት አሰራር መመቻቸቱን ጠቁመዋል ። "የተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ህክምናና ካሳ በወቅቱ ባለማግኘታቸው ለከፋ የአካል ጉዳትና ሞት እየተደረጉ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ናቸው። አጥፊውና ባለንብረቱ በህግ አግባብ ከመጠየቅ ይልቅ በጎን ተደራድረው ጉዳዩን የሚጨርሱበትንና የተጎጂዎች መብት እንዳይጠበቅ የሚያደርጉበት ሁኔታዎችን ለማስቀረት የዘመቻ ምዘገባው አሰተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። ለምዝገባ ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ደንበኞችን ለማስተናገድ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አሰራር ተዘርግቷል። የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን አገልግሎት ተመዝጋቢ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎችን መቆጣጠርና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከማድረግ አንፃር የተሰራው ስራ አጥጋቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ አድርሰው የሚሰወሩ ተሽከርካሪዎችን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድም ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል ። "ተጎጂዎች በወቅቱ የሚገባቸውን ህክምና ባለማግኘታቸው ለከፋ ጉዳት የሚጋለጡበት ሁኔታ እየሰፋ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዘመቻው የማይመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ማንኛውንም አገልግሎት እንዳይሰጡና መንገድ እንዳይጠቀሙ እንደሚደረግ አመላክተዋል ። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የምክክሩ መድረኩ ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለት ከተማ መስተዳደሮች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።