በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጨዋታዎች የሊጉ አሸናፊ ይለያል - ኢዜአ አማርኛ
በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጨዋታዎች የሊጉ አሸናፊ ይለያል
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2011 ኢዜአ የሊጉ አሸናፊ የሚለይበት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ። ሁሉም የሊጉ የማጠናቀቂያ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። እሁድ ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን ያስተናግዳል። ኮልፌ ከከምባታ ዱራሜ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በስፖርቱ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ31 ነጥብ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአንድ ነጥብ አንሶ የሚገኝ ሲሆን የእሁዱን ጨዋታ ካሸነፈ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ይሆናል። በወጣለት መርሃ ግብር መሰረት ሁሉንም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹን ያደረገው የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሸነፍ ወይም አቻ ወጥቶ በተመሳሳይ 32 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ የማሸነፍ እድል አለው። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ውጤታማ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ ሲሆን ይሄን ውጤታማ ጉዞውን በዋንጫ ለማጀብ የመጨረሻ ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠብቅበታል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከገጠመው ሽንፈት ውጪ ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከፌደራል ፖሊስ ከቀኑ ስምንት ሰዓት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጎንደር ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል። በ20ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ነገር ግን ከሁለት ወር ገደማ በፊት ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ራሱን ከውድድሩ ማግለሉ የሚታወቅ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ደንብ መሰረት መከላከያ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። በተጨማሪም በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የነበረው ቡታጅራ ከተማ በጨዋታ ሜዳዎች ባለመገኘት ተደጋጋሚ የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት በመሆኑ ምክንያት በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ከውድድሩ ውጪ እንዲሆን መደረጉም የሚታወስ ነው። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከውድድሩ ውጪ በመሆናቸው የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ውድድሩ ሲጀመር መከላከያ የመጀመሪያው አሸናፊ የነበረ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።